“ያቀድነውን ዕቅድ በማሳካታችን በጣም ተደስቻለሁ” አሰልጣኝ ሠርካለም ዕውነቱ

ሊጠናቀቅ አንድ ሳምንት የቀረው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ባህር ዳር ከተማን ቻምፒዮን አድርጓል፡፡ በሀዋሳ እየተደረገ በሚገኘው ውድድር ባህር ዳር ከተማ በዛሬው ዕለት ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚን 1ለ0 በመርታት የዲቪዚዮኑ ቻምፒዮን ከመሆኑ በዘለለ በ2014 ወደ አንደኛ ዲቪዚዮን መሸጋገሩም አረጋግጧል፡፡

ክለቡን እየመራች ለዚህ ክብር የበቃችው የቀድሞዋ የዳሽን ቢራ፣ ጥረት ኮርፖሬት እና የኢትዮጵያ ሴቶች ወጣት ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ የነበረችውና በአሁኑ ወቅት ክለቡን እየመራች የምትገኘው አሰልጣኝ ሠርካለም ዕውነቱ ከድሉ በኋላ ተከታዩን ሀሳብ ለሶከር ኢትዮጵያ ሰጥታለች፡፡

” የዓመቱ ውድድራችንን ቻምፒዮን ለመሆን አቅደን ነበር የጀመርነው፡፡ ያን ለማድረግም እንደ ክለብ ጥሩ ዝግጅት አድርገን ነበር የተነሳነው ይህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ትንሽ ከባድ ነበር፡፡ በኮሮና ምክንያት ተጫዋቾቹ በግላቸው ሲሰሩ የቆዩ ቢሆንም ከተሰበሰቡ በኋላ ወደ ትክክለኛው የአካል ብቃት ደረጃ ለማምጣት ከባድ ነበር። እሱ ላይ ትልቅ ሥራ ሠርተናል፡፡ እንደ አጠቃላይ ከነባር እና አዳዲስ ተጫዋቾች ጋር በመሆን አላማችንን እንዴት ማሳካት አለብን የሚለውን ተወያይተኝ ነበር የጀመርነው። ያ ነገር እንደ ቡድን ተሳክቶልናል። ቻምፒዮን እንድንሆን ትልቁ ምክንያት ተነሳሽነታችን፣ ኅብረታችን እንዲሁም ተጫዋቾቹ የሚሰጣቸውን ተግባር የመፈፀም ብቃት ነው።

“ይሄ ዓመት ከባድ ነበር። በሊጉ ብዙ ፈታኝ ጨዋታዎችን ነበር ያደረግነው። በአራት እና በአምስት ቀናት ልዩነት ነበር የሚደረጉት። በኮሮና ምክንያት ተጫዋቾች ከካምፕ እንዳይወጡ ጥንቃቄ እናደርግ ነበር። ብዙ ፈተናዎችን አልፈን ያቀድነውን ዕቅድ በማሳካታችን በጣም ደስ ብሎኛል።

“ቦሌ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በተናጠል ተፎካካሪ ሆነው ይታዩ እንጂ ሊጉ በጣም ጠንካራ ነበር፡፡ያልተጠበቁ ውጤቶች የሚመዘገቡበት በመሆኑ ካለፉት ዓመታት አንፃር የዘንድሮው በጣም የተለየ እና ጠንካራ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ክለቦች ለውጤታማነት ያደረጉት ተጋድሎም ውድድሩ ውበት እንዲኖረው ያደረጉ ነበሩ፡፡ በዛሬው ጨዋታ ከእኛ ቀድሞ ተከታያችን ነጥብ መጣሉ ለእኛ ተነሳሽነትን ጨምሮልን ነበር፡፡ እኛ የዘራነውን የምናጭድበት ቀን ስለነበር በደንብ ተዘጋጅተን ገብተን የለፋነውን ያሳካንበት ቀን ሆኗል።

“በመጨረሻም ልጆቼን ጥዬ መጥቼ መስዋዕት ከፍዬ መጥቼ ይሄን ውጤት በማየቴ ፈጣሪን አመስግነዋለሁ።”


© ሶከር ኢትዮጵያ