የአሰልጣኞች አስተያየት | ሰበታ ከተማ 2-2 ወላይታ ድቻ

በአቻ ውጤት ከተጠናቀቃው ጨዋታ በኋላ የተደረገው የአሰልጣኞች እና የሱፐር ስፖርት ቆይታ ይህንን ይመስላል።

አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ – ሰበታ ከተማ

በግቡ ስለመበሳጨታቸው

ከሁለተኛው ጎል ይልቅ የመጀመሪያው በጣም አበሳጭቶኛል። ምክንያቱም 2-0 እየመራን ነው። የተካላካዮቻችን ትኩረት ማነስ እና የግብ ጠባቂያችን የጊዜ አጠባበቅ ነው። አምስት ከሀምሳ ውስጥ ነው በግንባር ገጭቶ ያገባው ስለዚህ እዛ ጋር የተፈጠረ ችግር ነው። ሁለተኛው ላይ ግን ተጭነውን ፣ የሚችሉትን አድርገው ያስቆጠሩት ግብ ስለሆነ እሱ ብዙም አላበሳጨኝም። በተረፈ ግን ጨዋታውን የተቆጣጠርንበት መንገድ በጣም ጥሩ ነበር። ሁለተኛው አጋማሽ ውጤት ለማስጠበቅ ወደ ኋላ ማፈግፈጋችን ዋጋ አስከፍሎናል ። ይህንን በቀጣይ አስተካክለን እንደምንመጣ አስባለሁ።

ተጋጣሚያቸው ብልጫ ስለመውሰዱ

መዘናጋት ብቻ ነው። ተጋጣሚያችን ምንም የወሰደብን ብልጫ የለም። በአንፃሩ እኛ የተሻለ ብልጫ ነበረን። በተከላካዮቻችን መዘናጋት ነው ግቦች እንዲቆጠሩብን የሆነው። ይሄ እግር ኳስ ነው። እየመራህ ይገባብሀል ፣ እየተመራህ ታገባለህ ። ለምሳሌ እኛ ባለፈው እየተመራን ነው ያሸነፍነው። ስለዚህ አቻ መውጣታችንን በፀጋ እንቀበላለን።

ከዳኞች ጋር ስለተነጋገሩበት ምክንያት

ዳኝነቱን ዝም ብል ነው የሚሻለው። ጨዋታውን በትክልል እንዲቆጣጠሩት ብቻ ነበር መልዕክቴ። ከዚህ ውጪ ምንም ያልኩት ነገር የለም።

ምክትል አሰልጣኝ ዳዊት ሀብታሙ – ወላይታ ድቻ

ከተከላካዮች ጀርባ ክፍተት ስለመስጠታቸው

የመስጠት ጉዳይ ሳይሆን ጊዜው እና እንቅስቃሴው የፈጠረው ነው። ቅጣት ምት ተገኝቶ እሱን ለመሻማት በሄደበት ሰዓት እኛ መልዕክት እያስተላለፍን ነበር። ምክንያቱም እነሱ ፊታቸውን አዙረው ወደኛ ግብ ነው ያሉት እኛ ደግሞ ጀርባችንን ሰጥተን ነው። እና ትርፍ ሰዎች አንድ ለአንድ ሩጫ በሚደረግበት ሰዓት ነግረን ነበር ። በመልዕክቱ የመግባባት ችግር ስለነበር ሰበታ ያንን ጎል ማስቆጠር ችሏል።

በዕረፍት ስለተነጋገሩበት ጉዳይ

የገቡብን ጎሎች በራሳችን ድክመት እንጂ ብዙ ከባድ ሆነው አልነበረም። የአቋቋም እና የተነሳሽነት ችግር ስለነበር ነው። በኮቪድ ብዙ ተጫዋች ባጣንበት ወቅት ተነሳሽነታችን ከፍተኛ ነበር። ከዕረፍት በፊት ግን ይህ አልነበረም። በተነሳሽነታችን ላይ ነበር የተነጋገርነው። እንዲሁም የአቋቋም ችግራችን ላይ እና አብረን አጥቅተን አብረን መመለስ እንዳለብን ከአሰልጣኝ ቡድናችን ጋር ተነጋግረን ከዕረፍት በኋላ አግብተን እንደምንወጣ ባለሙሉ ልብ ነበረን ፤ ተሳክቶልናል።

አሰልጣኝ ዘላለም ስልክ ሳይደውሉ ቡድኑን እንዲመራ ዕድል ስለመስጠታቸው

ያው እኔ ከፊት የነበረው መስመር ላይ ስለነበርኩ ነው። እሱ ዕድሉን ለእኛ ነው የሰጠን። ከሜዳ ውጪ አንዳንድ ግንኙነቶች ነበሩን። በግብ ጠባቂ አሰልጣኝ በኩልም አንዳድንድ መልዕክቶች ነበሩ። አጠቃላይ የአሰልጣኝ ቡድን አባላቱ ለማስተካከል ጥረት አድርገናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ