ሪፖርት | ሲዳማ ቡና በሊጉ መትረፉን ሲያረጋግጥ ወልቂጤ ከተማ ደግሞ ከሊጉ የተሸኘ ሌላኛው ክለብ ሆኗል

ሲዳማ ቡና ጅማ አባጅፋርን 4-1 ማሸነፉን ተከትሎ በሊጉ መትረፉን ሲያረጋግጥ ወልቂጤ ከተማ ደግሞ ከሊጉ የተሰናበተ ሦስተኛው ክለብ ሆኗል።

የሲዳማ ቡናው ዋና አሠልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ቡድናቸው ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ሦስት አቻ ከተለያየበት ስብስብ የሦስት ተጫዋቾችን ለውጥ አድርገው ወደ ሜዳ ገብተዋል። በዚህም ቅጣት ላይ የሚገኘው ፋቢያን ፋርኖሌን በግቦቹ መካከል በፍቅሬ ወልዴ እንዲሁም ሀብታሙ ገዛኸኝ እና ፈቱዲን ጀማልን በግርማ በቀለ እና ቢንያም በላይ ተክተዋል። ከሊጉ መውረዳቸውን ቀድመው ያረጋገጡት ጅማ አባ ጅፋሮችም በተመሳሳይ ከባህር ዳር ከተማ ጋር ነጥብ ከተጋራው ቋሚ ስብስብ ሦስት ተጫዋቾች ለውጠዋል። በዚህም አሠልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ቅጣት ላይ የሚገኘው ስዩም ተስፋዬን ጨምሮ ዋውንጎ ፕሪንስ እና ራሂም ኦስማኖን በሳዲቅ ሴቾ፣ ኤልያስ አታሮ እና ወንድማገኝ ማርቆስ ተክተዋል።

በጨዋታው ከፍተኛ የማሸነፍ ፍላጎት የሚነበብባቸወ የሲዳማ ቡና ተጫዋቾች ከጀምሩ አንስሮ ጅማ ላይ ጫና ማሳደር ይዘዋል። በተለይም በሁለቱ መስመሮች በኩል ፍጥነት የታከለበት እንቅስቃሴ በማድረግ ግብ ለማስቆጠር ሲታትሩ ነበር። ውጥናቸውም ሰምሮ ገና በ6ኛው ደቂቃ መሪ የሆኑበትን ኳስ ከመረብ ጋር አዋህደዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም የቀኝ መስመር ተከላካዩ አማኑኤል እንዳለ ጥሩ ኳስ ለኦኪኪ አፎላቢ አቀብሎት ቁመታሙ አጥቂ በግንባሩ ጎል አስቆጥሯል።

በቁጥር በዝተው ለመከላከል ያሰቡ የሚመስሉት ጅማዎች ግብ ካስተናገዱ ከአስር ደቂቃዎች በኋላ በራሳቸው በኩል የመጀመሪያውን ጥቃት በፈጣን መልሶ ማጥቃት ፈፅመዋል። በዚህም ወደ ቀኝ ባዘነበለ ቦታ ላይ በመሮጥ ከተመስገን ደረሰ የተቀበለውን ኳስ ሳዲቅ ሴቾ ለመጠቀም ጥሮ ለጥቂት ወጥቶበታል። ከዚህ ደቂቃ በኋላም ቡድኑ በአንፃራዊነት በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ ሻል ብሎ ታይቷል። 

በተቃራኒው የሚፈልጉትን ገና በጊዜ ያገኙት ሲዳማ ቡናዎች ደግሞ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ሲሰነዝሯቸው የነበሩትን ጥቃቶች ጋብ አድርገው መንቀሳቀስን መርጠዋል። ይህ ቢሆንም ግን አልፎ አልፎ ረጃጅም ኳሶችን በመጠቀም ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ታትረዋል። በዚህ እንቅስቃሴም በ38ኛው ደቂቃ ቡድኑ መሪነቱን ወደ ሁለት ከፍ ያደረገበትን ጎል አግኝቷል። በተጠቀሰው ደቂቃም ግርማ በቀለ ከርቀት ያሻገረውን ኳስ ቢኒያም በላይ በደረቱ ለኦኪኪ ሲያመቻቸው ኦኪኪ ግብ ለማስቆጠር የሚመቸውን ቦታ ከፈለገ በኋላ በግራ እግሩ የመታው ኳስ መዳረሻው አቡበከር ኑሪ ጀርባ የሚገኘው መረብ ሆኗል። በቀሪዎቹ ደቂቃዎችም ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠር አጋማሹ ሲዳማን መሪ አድርጎ ተገባዷል።

በመጀመሪያው አጋማሽ አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ያላደረጉት ጅማ አባጅፋሮች በሁለተኛው አጋማሽ በተሻለ ወደ ግብ ለመድረስ የአማካይ መስመር ተጫዋች በማስወጣት የአጥቂ ባህሪ ያለው ተጫዋች አስገብተዋል። ይሄ ሀሳባቸው ግን እምብዛም ሜዳ ላይ ሲሳካ አልታየም። ሲዳማ ቡናዎች ደግሞ በአብዛኛው ጨዋታውን መቆጣጠር ላይ ትኩረት በማድረግ ሲንቀሳቀሱ ተስተውሏል። በዋናነትም ኳስን በትዕግስት በመቀባበል ጨዋታውን ቀጥለዋል። ይሄ ቢሆንም ግን በ60ኛው ደቂቃ ዳዊት ተፈራ ከሳጥኑ ጫፍ ሆኖ በሞከረው እና የግብ ዘቡ አቡበከር ኑሪ በመለሰው ኳስ ሦስተኛ ጎል ለማግኘት ጥረዋል።

ጨዋታው ቀጥሎም በ70ኛው ደቂቃ ጅማ አባጅፋር የመጀመሪያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ወደ ጎልነት ቀይሮታል። በዚህ ደቂቃም ኤሊያስ አታሮ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ተመስገን ደረሰ በሰንደይ ሙቱኩ እና መሐሪ መና መሐል በመገኘት በግንባሩ ግብ አስቆጥሯል። ለተቆጠረባቸው ጎሎ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ያላመነቱት ሲዳማ ቡናዎች ከአንድ ደቂቃ በኋላ ሦስተኛ ጎል አስቆጥረዋል። በዚህም የቡድኑን ሁለት ጎሎች አስቆጥሮ የነበረው ኦኪኪ ተቀይሮ ወደ ሜዳ ከገባው ዩናስ ገረመው የተቀበለውን ኳስ የግል ጥረቱን አክሎበት ሐት-ትሪክ ሰርቷል።

በ81ኛው ደቂቃ ማማዱ ሲዲቤን ቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ይገዙ ቦጋለ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ከዳዊት ተፈራ የደረሰውን ኳስ በግብ ጠባቂው አቡበከር አናት ላይ በመላክ ለቡድኑ አራተኛ ጎል አስቆጥሯል። ጨዋታው ከቁጥጥራቸው ውጪ የሆነባቸው ጅማዎች በቀሪዎቹ ደቂቃዎች የግቡን ልዩነት ለማጥበብ ቢታትሩም ስኬታማ ሳይሆኖኑ ቀርተዋል። ሲዳማ ቡናም በሊጉ መትረፉን ያረጋገጠበትን ጎሎች በተከታታይ ካስቆጠረ በኋላ መዝናኖት በተሞላበት ስሜት ቀሪዎቹን ደቂቃዎች ተጫውቷል። ጨዋታውም ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠርበት በሲዳማ ቡና 4-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።


ውጤቱን ተከትሎ የአሠልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ቡድን ነጥቡን 28 በማድረስ በሊጉ መትረፉን አረጋግጧል። በተቃራኒው ነጥቡን ከማሳደግ ውጪ የደረጃ ለውጥ እንደማያደርግ አውቆ ጨዋታውን የጀመረው ጅማ አባጅፋር ደግሞ በ15 ነጥቦች ያለበት 12ኛ ደረጃ ላይ ፀንቶ ተቀምጧል።