ቅዱስ ጊዮርጊስ በ17 ዓመት በታች ውድድር ይሳተፋል

በአዲስ አበባ ከ17 ዓመት በታች ውድድር ላይ ያልተሳተፈው የቅዱስ ጊዮርጊስ ታዳጊ ቡድን በቀጣይ በሚደረገው ሀገር አቀፍ ውድድር እንደሚሳተፍ ተረጋግጧል።

በአሰልጣኝ ሳምሶን ሙሉጌታ (ፍሌክስ) የሚመራው ይህ የታዳጊ ቡድን ምንም እንኳን አስቀድሞ በአዲስ አበባ ከ17 ዓመት ውድድር ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት የነበረው ቢሆንም ውድድሩ የኮቪድን ፕሮቶኮል ያልጠበቀ ነው በሚል ራሱን ማግለሉ ይታወቃል። የታዳጊ ቡድኑ በውድድሩ ላይ አይሳተፍ እንጂ ሳይበተን ታዳጊዎችን በመያዝ በሜዳም ከሜዳም ውጭ የተለያዩ ተግባራትን በመስራት ዝግጅት ሲያደርጉ ቆይቷል። በቅርቡ ደግሞ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አወዳዳሪነት በሀዋሳ ከተማ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው ከ17 ዓመት በታች የፕሪምየር ሊግ ውድድር ላይ እንደሚሳተፍ ተረጋግጧል።

ይህን አስመልክቶ የቀድሞ የፈረሰኞቹ ጠንካራ ተከላካይ እና የአሁኑ የታዳጊ ቡድኑ አሰልጣኝ ሳምሶን ሙሉጌታ ስለ ዝግጅታቸው ለሶከር ኢትዮጵያ ይህን ተናግሯል።

“የአዲስ አበባን ውድድር ለመሳተፍ ፈልገን የነበረ ቢሆንም ከኮቪድ ፕሮቶኮል አንፃር ሳንሳተፍ ቀርተናል። አሁን ሀዋሳ ላይ የሚዘጋጀው ውድድር የኮቪድ ፕሮቶኮልን በጠበቀ ሁኔታ በቂ የMRI ምርመራ የሚደረግበት እንዲሁም ሁሉም ቡድኖች በአንድ ላይ የሚሰባሰቡበት በመሆኑ እና ለውድድሩ ትኩረት የተሰጠበት በመሆኑ እኛም የምንሳተፍ ይሆናል። ውድድሩ የሚጀመርበት ቀን ለጊዜው መቼ እንደሆነ ባናቀውም በበቂ ሁኔታ ክለቤም ትኩረት ሰጥቶበት እየተዘጋጀን እንገኛለን።

” የኔ ትልቁ ዓላም ውድድሩ ላይ የግድ ቻምፒዮን መሆን አይደለም። እኔ ከስር ጀምሬ እስከ ዋናው ቡድን የሰራሁትን ታሪክ አሁን ያሉትም ልጆች ከታች ጀምረው እስከ ዋናው ቡድን ድረስ ጥሩ ጥሩ ልጆችን መፍጠር ነው። በዲሲፕሊን የታነፁ ለጊዮርጊስ ማልያ ፍቅር ያላቸው። ጠንካራ እና አልሸነፍ ባይነት የተላበሱ ታዳጊዎችን በማብቃት ለዋናው ቡድን ግብአት የሚሆኑ ልጆች ማዘጋጀት የእኔ የመጀመርያው ትልቁ ዓላማዬ ነው። ከአስራ ሰባት ዓመት በታች ቡድን ዋንጫ አግኝተህ ልጆቹ ወደ ዋናው ቡድን የማታሳድግ ከሆነ ትርጉም የለውም። ስለዚህ በሥርዓት የታነፁ ኳሱን የሚወዱ የማልያ ፍቅር ያላቸውን ልጆች ለክለቤ ብቻ ሳይሆን ለሀገሬ ማብቃት ነው የኔ ትኩረት። ይህንንም አሁን ባሉኝ ልጆች እየተመለከትኩ ነው። በቀጠይም ትኩረት ሰጥተን የምንሰራ ይሆናል።”