የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሁለተኛ የአቋም መፈተሻ ጨዋታውን ዛሬ አከናውኗል

በሀገራችን በሚስተናገደው የሴካፋ ውድድር ላይ የሚካፈለው የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ከሰዓት ሁለተኛ የአቋም መፈተሻ ጨዋታውን አድርጎ ግማሽ ደርዘን ጎል አስቆጥሯል።

ከሰኔ 26 እስከ ሐምሌ 12 በሚደረገው የምስራቅ እና መካከለኛው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከሰኔ 4 ጀምሮ ዝግጅቱን እያደረገ እንደሆነ ይታወቃል። በካፍ የልህቀት ማዕከል እና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሜዳ ከሚደረገው ልምምድ በተጨማሪም ቡድኑን ብቁ ለማድረግ አሠልጣኝ ውበቱ አባተ እና ረዳቶቹ በሀገር ወስጥ ከሚገኙ ክለቦች ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ እያደረጉ ይገኛሉ። ባሳለፍነው ቅዳሜም ቡድኑ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር መጫወቱ የሚታወስ ሲሆን ዛሬ ደግሞ በአዲስ አበባ ከፍተኛ ዲቪዚዮን ከሚወዳደረው ምህረት ክለብ ጋር በአዲስ አበባ ስታዲየም ሁለተኛ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ አድርጓል።

ለሁለት ተከፍሎ የዛሬውን ጨዋታ ባደረገው ቡድን ውስጥም ፅዮን መርዕድ፣ አማኑኤል እንዳለ፣ ሰለሞን ወዴሳ፣ ፀጋሰው ድማሙ፣ ዮሐንስ ሴጌቦ፣ በረከት ወልዴ፣ ዳዊት ተፈራ፣ አብዱልሀፊዝ ቶፊክ፣ ቸርነት ጉግሳ፣ መስፍን ታፈሰ እና ብሩክ በየነ በመጀመሪያውን አጋማሽ ተጫውተዋል። እጅግ ከፍተኛ የጨዋታ ብልጫ ኖሮት የተጫወተው የአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የመጀመሪያ ስብስብም ኳስን በማንሸራሸር ቶሎ ቶሎ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲታትር ታይቷል። በዚህም ጨዋታው እንደተጀመረ መስፍን ታፈሰ ባስቆጠረው ጎል መሪ ሆኗል። ከዛም ከቀኝ መስመር የተሻገረውን ኳስ የምህረት ቡድን ተከላካይ ፈይሰል ዲኖ በራሱ ላይ እንዲሁም መስፍም ታፈሰ በተመሳሳይ ከቀኝ መስመር የተመቻቸለትን ኳስ በጥሩ ሁኔታ ወደ ጎልነት ቀይሮት ቡድኑ ሁለት ተከታታይ ጎሎችን አግኝቷል። አጋማሹ ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት ደግሞ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ቸርነት ጉግሳ በተከላካዮች መሐል የደረሰውን ኳስ በጥሩ ቅልጥፍና መረብ ላይ በማሳረፍ አራተኛ ጎል ተቆጥሯል።

በሁለተኛው አጋማሽ ሙሉ ተጫዋች ቀይረው ወደ ሜዳ የገቡት አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ፋሲል ገብረሚካኤል፣ ኃይሌ ገብረትንሳይ፣ መናፍ አወል፣ እያሱ ለገሠ፣ ኃይለሚካኤል አደፍርስ፣ ሀብታሙ ተከስተ፣ ዊሊያን ሠለሞን፣ ወንድማገኝ ኃይሉ፣ ሙህዲን ሙሳ፣ ይገዙ ቦጋለ እና አቡበከር ናስርን ወደ ሜዳ አስገብተዋል። ይሄም ስብስብ ከኳስ ጋር ዘለግ ያለ ጊዜ ሲያሳልፍ አስተውለናል። በአጋማሹም ወንድማገኝ ኃይሉ ቀድሞ ግብ ሲያስቆጥር አቡበከር ናስር ደግሞ በረጅሙ የተላከለትን ኳስ በግብ ጠባቂው አናት ወደ ግብነት ቀይሮ 6ኛ ጎል ተቆጥሯል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ 20 ደቂቃዎች ሲቀሩት አሠልጣኝ ውበቱ ግብ ያስቆጠረው አቡበከርን እና ሙህዲን አስወጥተው ዱሬሳ ሹቢሳን እና ስንታየሁ መንግስቱን ወደ ሜዳ አስገብተዋል። በቀሪ ደቂቃዎችም ቡድኑ ብልጫ ኖሮት ተጫውቶ ጨዋታውን አገባዷል።

በዛሬው ጨዋታ በመጀመሪያው ቡድን አራት ለምንም በሁለተኛው ቡድን ደግሞ ሁለት ለምንም በአጠቃላይ ስድስት ለምንም ያሸነፈው ብሔራዊ ቡድኑ በነገው ዕለት ውድድሩ ወደሚደረግበት ባህር ዳር ከተማ እንደሚያቀና ሰምተናል።