የሁለተኛ ቀን ወሳኝ ሦስት ጨዋታዎች ዳሰሳ

የትግራይ ክልል ክለቦች በሊጉ ካልተሳተፉ እነርሱን ለመተካት የሚደረገው ፍልሚያ ነገ በሦስት ጨዋታዎች ቀጥሎ ይደረጋል።

ባሳለፍነው ዓርብ የተጀመረው እና ስድስት ክለቦችን የሚያሳትፈው ውድድር ነገ በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ሦስት ጨዋታዎችን በማስተናገድ ቀጥሎ ይውላል። ነገ ከሚደረጉት ጨዋታዎች መካከልም በመጀመሪያው ግጥሚያ ተጋጣሚዎቻቸውን ያሸነፉት አዳማ እና ኮልፌ እርስ በእርስ ይገናኛሉ። ይሄንን ተጠባቂ ጨዋታ ጨምሮ የነገ መርሐ-ግብሮችን እንደሚመለከተው ዳሰናቸዋል።

👉አዳማ ከተማ ከ ኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከ (3:00)

ሁለት የተለያየ የጨዋታ መንገድ ያላቸው አዳማ ከተማ እና ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ነገ የሁለተኛውን ዙር የመጀመሪያ ጨዋታ 3 ሰዓት ሲል ያከናውናሉ፡፡ ከሦስት ቀናት በፊት ውድድሩ ሲጀመር ተጋጣሚዎቻቸውን በተመሳሳይ የጎል መጠን (1-0) በመርታት በድል የጀመሩት ሁለቱ ቡድኖች ከድል መልስ ነገ የሚፋጠጡበት ጨዋታ ትልቅ ግምት አግኝቷል፡፡ በፕሪምየር ሊጉ የደረጃ ሰንጠረዡን ግርጌ ይዞ የፈፀመው አዳማ ከተማ ባለፈው ኢትዮ ኤሌክትሪክን ባሸነፈበት ፈጣን የሽግግር እንቅስቃሴ እና ረጃጅም ኳሶችን ለአጥቂዎች የማድረስ አጨዋወት ራሱን ቃኝቶ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይታሰባል። ለተቃራኒ ቡድን ተከላካዮች ፍጥነታቸው ፈታኝ እንደሆነ የታየው የአዳማ አጥቂዎች በነገው ጨዋታ ምናልባት አብዲሳ ጀማል ከጉዳት ከተመለሰላቸው የኮልፌ ተከላካዮች ላይ ሥራ አብዝተው ሊጫወቱ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ኳስን መሠረት ባደረገ መንገድ የሚጫወቱት ኮልፌዎች የባለፈውን ሜዳ አካሎ የመጫወት ባህሪ ነገም ከደገሙ የአዳማ የኋላ መስመር ላይ ስጋት ሊፈጥሩ ይችላሉ።

ኳስን መሠረት ባደረገ አጨዋወት ሳቢ እንቅስቃሴ በሀምበሪቾው ጨዋታ ያሳየው የአሰልጣኝ መሀመድኑር ክለብ ኮልፌ ቀራኒዮ ሜዳው ወደ ጎን በመለጠጥ በመስመር በይበልጥ የሚያደርጉትን ጥቃት ነገም ከደገሙ በቀላሉ ተጋላጭ ለሆነው የአዳማ ተከላካይ ክፍል የራስ ምታት መሆናቸው አይቀሬ ይመስላል፡፡ በሀምበሪቾ ጨዋታ ሁለቱን መስመሮች በሚገባ በአንዋር ዱላ እና ብሩክ ሙሉጌታ አማካኝነት ሲጠቀሙ የነበሩት ኮልፌዎች ነገም በመሐል ሜዳ ተጫዋቾቹ ደሳለኝ ወርቁ እና አቡበከር ሻሚል ቅብብል አዳማን እንደሚያስጨንቁ ይታሰባል። ነገር ግን ከማጥቃት ወደ መከላከል ባለ የሽግግር ጊዜ ያሳዩት የነበረውን ድክመት ከተደገመ ለአዳማ ፈጣን አጥቂዎች በቀላሉ እጅ ሊሰጡ ይችላሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

👉ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ጅማ አባጅፋር (7:30)

ሽንፈት እና አቻ ውጤትን ይዘው ምሳ ሰዓት የሚገናኙት ሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ ሙሉ ነጥባቸውን ለማሳካት ወደ ሜዳ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በአሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና የሚመራው ኢትዮ ኤሌክትሪክ የሜዳውን ስፋት በይበልጥ ሲጠቀሙ ይታያል። በተለይ በአዳማው ጨዋታ ሳሙኤል ታዬን ማዕከል አድርገው ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ የነበረበት መንገድ አጀማመሩ ያማረ ይመስል የነበረ ቢሆን የኤርሚያስ ኃይሉ እና የየተሻ ግዛው ፍፁም ደካማ የአጨራረስ ብቃት ቡድኑን ዋጋ አስከፍሎታል። ይሄ ክፍተትም በነገው ዕለት የሚደገመው ከሆነ ቡድኑ አጣብቂኝ ውስጥ ሊወድቅ ይችላል፡፡ ነገር ግን ተጫዋቾቹ ሳጥን ውስጥ ለመድረስ የማይቸገሩ በመሆኑ ይሄን የአጨራረስ ክፍተት ካረሙ ነገ የመጀመሪያ ድላቸውን ያሳካሉ የሚል እምነት ይኖራል፡፡

ረጃጅም ኳስን መከተል ምርጫ ያደረጉት ጅማ አባጅፋሮች አብዛኛዎቹ የማጥቂያ መንገዳቸው ተገማች በመሆኑ በቀላሉ ኳስን ለመጫወት በሚሞክሩት ኤሌክትሪኮች እንዳይበለጡ ያሳጋል፡፡ እርግጥ ቡድኑ የተመስገን ደረሰን እና ራሂም ኦስማኖን ፍጥነት ለመጠቀም መጣሩ ስህተት ባይሆንም ኳሶችን ለእነርሱ ለማድረስ የሚጥርበት መንገድ ተመሳሳይ መሆኑ ለተጋጣሚ ቡድን ቀላል እንዳይሆን ያሰጋል። በዋናነት ግን የቡድኑ የፊት መስመር ላይ የሚታየው የአጨራረስ ብቃት ችግር ነገም የሚደገም ከሆነ ቡድኑ ችግር ውስጥ ሊወድቅ ይችላል። ምንም ቢሆን ምንም ግን የቡድኑ ጠጣር የተከላካይ ክፍል ለኢትዮ ኤሌክትሪክ ፈተና ሊሆን እንደሚችል ይታሰባል።

👉ወልቂጤ ከተማ ከ ሀምበሪቾ ዱራሜ (10:00)

በአሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ብቻ እየተመራ ያለ ረዳት አሰልጣኞች ሁለተኛ ጨዋታውን የሚያደርገው ወልቂጤ ከተማ ከጅማ አባጅፋር ጋር በነበረው ጨዋታ ድል ባይቀናውም ጥሩ ሲንቀሳቀስ ታይቷል። ነገም እንደ ዓርቡ ተመሳሳይ የማጥቃት አጨዋወት ይዞ ወደ ሜዳ የሚገባ ከሆነ ለሀምበሪቾ ዱራሜ ከባድ ተጋጣሚ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በተለይ መሀል ሜዳ ላይ በተደራጀ መልኩ በፍሬው ሠለሞን እና አብዱልከሪም ወርቁ ጥምረት እንዲሁም መስመር ላይ ባሉት አሜ መሐመድ እና አቡበከር ሳኒ ኳስ ወደ ሳጥን ሰብሮ ለመግባት የሚጥረው ቡድኑ ነገም ይሄንን ስልት ለመድገም እንደሚያልም ይታሰባል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በተደጋጋሚ አጥቂው አህመድ ሁሴን የሚታይበት የውሳኔ አሰጣጥ ችግር ነገም የሚደግም ከሆነ ቡድኑ ሦስት ነጥብ ለማግኘት ሊቸገር ይችላል። ከዚህ ውጪ በማጥቃቱ ረገድ ቡድኑ ጥሩ ቢሆንም የመከላከል አወቃቀሩ ግን ለሀምበሪቾ ተጫዋቾች ከባድ ጊዜ እንዲሰጥ ተደርጎ መሰራት ይገባዋል።

ብዙ ክፍተቶቹ በኮልፌው ጨዋታ የታየው ሀምበሪቾ ዱራም ነገ ብዙ መሻሻል አሳይቶ ወደ ሜዳ ካልገባ ሊቸገር ይችላል። እርግጥ የቡድኑ የመስመር አጨዋወት የተሻለ ቢሆንም በመከላከል ቅርፅ ያለው አደረጃጀት ጥሩ አለመሆን ራሱን ችግር ውስጥ እንዳይከተው አስግቷል። በተለይ ቡድኑ የጅማን የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት እንዴት ይመክታል አልፎስ ከላይ የጠቀስነውን የተከላካይ ክፍል እንዴት ሰብሮ ይገባል የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል። ይህ ቢሆንም ግን ቡድኑ አጥቂው ቢኒያም ጌታቸው ከዳግም በቀለ ጋር ያለውን ጥምረት ካስተካከለ እና የተከላካይ ክፍሉ ላይ ያለበትን ክፍተት ከደፈነ ውጤታማ ሊሆን ይችላሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡