የአሠልጣኞች አስተያየት | ኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከ 0-3 ጅማ አባጅፋር

በጅማ አባጅፋር ሦስት ለምንም አሸናፊነት ከተጠናቀቀው የረፋዱ ጨዋታ በኋላ አሠልጣኞች የድህረ-ጨዋታ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ፀጋዬ ኪዳነማርያም – ጅማ አባጅፋር

ጨዋታው እንዴት ነበር?

ጨዋታው ጥሩ ጨዋታ ነበር። በፕሪምየር ሊግ የነበረንን አቋም ለመድገም ሞክረናል። በተቻለ አቅም ሥራዎችን ሰርተን ጠንክረን ወደ ሜዳ ለመግባት ጥረናል። እንደምታቀው በሁለት ሳምንት ጨዋታዎች ወደ ፕሪምየር ሊግ የሚገባበት ውድድር ነው። የመጀመሪያዎቹ አንድ ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ ትንሽ ከበድ ያሉ ነበሩ። ከዛ ግን እየሰራን ተስተካክለን ለመቅረብ ሞክረናል። የዛሬው ተጋጣሚያችን ኮልፌ ኳስ ይዞ የሚጫወት ቡድን ነው። በቴክኒኩም ረገድ የተሻሉ ተጫዋቾች እንዳሏቸው እናውቃለን። ከዚህ መነሻነት የነበራቸውን አቅም አውጥተው እንዳይጫወቱ ለማድረግ ሞክረናል። ከነበረን የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ እና ብልጫ አንፃር ድሉ ይገባን ነበር። በአጠቃላይ ጥንቃቄ የተሞላበት አጨዋወት ተከትለን ጨዋታውን አሸንፈን ወጥተናል።

የጨዋታ እቅዳችሁ ምን ነበር?

እኛ የራሳችን አጨዋወት አለን። ግን እንዳልኩት እነሱ አቅማቸውን እንዳያወጡ አድርገን ተጫውተናል። በተለይ ደግሞ ኳስ ስንነጥቅ የምንከተለው አጨዋወት ድንቅ ነበር። ኳሶችን ቶሎ መንጠቅ፣ ማፍጠን እና ሜዳውን አስፍቶ መጠቀም ሞክረናል። ሜዳ ላይ ከታየው እንቅስቃሴም አንፃር ውጤቱ ይገባናል።

ስለ ቀጣዩ ጨዋታ?

ውድድሩ አላለቀም። አንድ ጨዋታ ይቀረናል። ቀጣይ ተጋጣያችን አዳማ ከተማ ነው። አዳማም አሸንፎ የመጣ ክለብ ነው። ለዚህ ጨዋታ ጠንክረን ለመዘጋጀት እንሞካራለን። በሊጉም ለመቆየት ከፍተኛ ጥረት እናደርጋለን።

መሐመድኑር ንማ – ኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከ

ስለ ጨዋታው?

ጨዋታው እንደጠበቅነው አይደለም። ጨዋታው ላይ የሀይል አጨዋወት ይበዛ ነበር። ዳኛውም የሀይል አጨዋወት ፈቅዶ ነበር። በዚህም ወሳኝ ተጫዋቾቻችን ተጎዱብን። ሌላው የመከላከል ሽግግራችን ድክመት ነበረበት። በዚህ ምክንያት ተሸንፈን ወጥተናል።

በተጋጣሚ ጥንካሬ ነው ወይስ በራሳችሁ ድክመት የተሸነፋችሁት?

ያልኩት ክፍተት ነበር። ግን የእኛም ተጫዋቾች የመረጋጋት ችግር ነበረባቸው። ይሄም ክፍተት አምጥቷል።

እየተመሩ ግብ ጠባቂ ስለመቀየራቸው?

ግብ ጠባቂው ህመም ነበረበት። ከዚህ በተጨማሪም ሳይኮሎጂካሊ ወርዶ ነበር። ከዚህ መነሻነት ነው የቀየርነው።