ሪፖርት | ጅማ አባጅፋር ተከታታይ ድሉን አስመዝግቦ ደረጃውን አሻሽሏል

ከድል መልስ የመጡትን ኮልፌ ቀራኒዮ እና ጅማ አባጅፋርን ያገናኘው የአራተኛ ዙር የመክፈቻ ጨዋታ ጅማ አባጅፋርን አሸናፊ አድርጎ ተጠናቋል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክን ሁለት ለምንም ረተው ለዛሬው ፍልሚያ የተዘጋጁት ኮልፌዎች ሦስት ነጥብ ካሳኩበት ጨዋታ አንድ ተጫዋች ብቻ ለውጠዋል። በዚህም አሠልጣኝ መሐመድኑር በግብ ብረቶቹ መካከል አዲሱ ቦቄን በኃይማኖት አዲሱ ተክተው ቡድናቸውን ወደ ሜዳ አስገብተዋል። እንደ ኮልፌ ሁሉ ድል ተቀዳጅተው የዛሬውን ጨዋታ ሲጠባበቁ የነበሩት ጅማዎች በተመሳሳይ አንድ ለውጥ ብቻ አድርገው ጨዋታውን ቀርበዋል። በዚህም የአጥቂ መስመር ተጫዋቹ ሳዲቅ ሴቾ አርፎ ግዙፉ ራሂም ኦስማኖ በቋሚነት ጨዋታውን ጀምሯል።

በስታዲየሙ በነበረው ቀዝቃዛ አየር እና መጠነኛ ዝናብ ታጅቦ የተጀመረው ጨዋታ ከአየር ንብረቱ በተቃራኒ ጅማሮው ላይ ሞቅ ባለ እንቅስቃሴ ተቃኝቶ መደረግ ይዟል። በተለይ ጅማ አባጅፋር ከመጀመሪያው ደቂቃ አንስቶ ቀዳሚ ሊሆኑ የሚችሉበትን ግብ ለማግኘት ሲታትሩ ነበር። በዚህም ጨዋታው በተጀመረ በአራተኛው ደቂቃም ሁለት እጅግ ለግብ የቀረቡ አጋጣሚዎችን በሰከንዶች ልዩነት ከቆመ ኳስ አድርገዋል። በቅድሚያ ዋውንጎ ፕሪንስ ያሻገረውን የመዓዘን ምት ዋለልኝ ገብሬ አግኝቶት ወደ ግብነት ለመቀየር ቢጥርም ተከላካዮች በጥሩ ቅልጥፍና ኳሱን አምክነውታል። የወጣውን ኳስ ዳግም ፕሪንስ ወደ ሳጥን አሻግሮት ራሂም ኦስማኖ በግንባሩ ጎል ሊያደርገው ተቃርቦ ነበር።

በጨዋታው ጅማሮ ላይ ብልጫ የተወሰደባቸው ኮልፌዎች የጅማን ረጃጅም እና ተሻጋሪ ኳሶች በሚገባ መቆጣጠር ተስኗቸው ጨዋታው ቀጥሏል። በ11ኛው ደቂቃም ከግራ መስመር የተሻገረውን ኳስ ተመስገን ደረሰ በሩቁ ቋሚ ሆኖ አግኝቶት ግብ ሊያስቆጥርባቸው ነበር። ከዚህኛው ሙከራ በኋላ ግን ቡድኑ በተሻለ ኳስን ለመቆጣጠር ሲታትር ታይቷል። ቡድኑ በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ የተሻለ ቢመስልም ጅማዎች የሚሰነዝሩትን የአየር ጥቃት ግን አሁንም ከምንጩ ማስቀረት አልቻለም። የመጀመሪያው አጋማሽ የውሃ እረፍት ተደርጎ እንደተጀመረ የቅጣት ምት ያገኙት ጅማዎች አጋጣሚውን በስዩም ተስፋዬ አማካኝነት አሻምተውት በአምበላቸው መላኩ ወልዴ አማካኝነት ወደ ግብ ሊቀይሩት ዳድተው ነበር።

ጨዋታው 37ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ግብ አስተናግዷል። ግብ ከመቆጠሩ ከሰከንዶች በፊት ወደ ቀኝ ባዘነበለ ቦታ ላይ የቅጣት ምት ያገኙት ኮልፌዎች አጋጣሚውን በኪሩቤል ወንድሙ አማካኝነት ወደ ግብ ለመቀየር ጥረው መክኖባቸዋል። ይህንን የቅጣት ምት የተቆጣጠረው የግብ ዘቡ አበቡበከር ኑሩ ወዲያው ያገኘውን ኳስ ለኦስማኖ አሻግሮለት ግብ ተገኝቷል። ቁመታሙ አጥቂም ከርቀት የተመታውን ኳስ ከተከላካዮች ጋር ታግሎ ካገኘ በኋላ ከሳጥ ውጪ ግብ ጠባቂው አዲስ ቦቄን አቁሞ ግብ አስቆጥሯል። ለተቆጠረባቸው ጎል ምላሽ ለመስጠት ያሰቡ የሚመስሉት ኮልፌዎች ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ መላኩ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘን ኳስ በመጠቀም በብሩክ ሙሉጌታ አማካኝነት አቻ ለመሆን ጥረት አድርገዋል። 

ሙሉ የአጋማሹ ደቂቃ ተጠናቆ በተጨመረው ደቂቃም አቡበከር ሸሚል ከሳጥን ውጪ ሌላ ሙከራ አድርጎ ነበር። ነገርግን የመጨረሻ ደቂቃዎች የቡድኑ ሙከራ ፍሬ ሳያፈራ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል። አጋማሹ ተጠናቆ ተጫዋቾች ወደ መልበሻ ክፍል በሚያመሩበት ሰዓት የኮልፌው የግብ ጠባቂዎች አሠልጣኝ ጥላሁን አበበ ከዕለቱ ዳኛ ጋር በፈጠሩት ግብግብ በቀይ ካርድ ከሜዳ እንዲወጡ ተደርጓል።

በሁለተኛው አጋማሽ ሻል ብለው የመጡ የሚመስሉት ኮልፌዎች ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን ጎል ለማግኘት መልፋት ይዘዋል። ጅማዎች በበኩላቸው በእጃቸው የገባውን ሦስት ነጥብ አሳልፎ ላለመስጠት ወደ ራሳቸው የግብ ክልል በአንፃራዊነት አፈግፍገው ተጫውተዋል። አልፎ አልፎ ግን ከቆመ ኳስ እና በመልሶ ማጥቃት የሚገኙ አጋጣሚዎችን በመጠቀም ተጨማሪ ጎል ለማግኘት ጥረት አድርገዋል። በዚህም 50ኛው ደቂቃ ላይ አቡበከር ከሚል የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የቅጣት ምት መላኩ ለመጠቀም ሞክሮ የግቡ ቋሚ ውጥኑን አምክኖበታል። ኮልፌዎች ደግሞ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ሁለት ጥሩ ጥቃቶችን ፈፅመዋል። በቅድሚያም አቡበከር ከሚል ፍጥነቱን ተጠቅሞ ከተከላካይ ጀርባ ሮጦ ያገኘውን ኳስ ወደ ግብ ሊቀይረው ብሎ ሲከሽፍበት ከደቂቃ በኋላ ደግሞ የአማካይ መስመር ተጫዋቹ አንዋር ዱላ ከሳጥን ውጪ ጥሩ ጥቃት ፈፅሞ ነበር።

የኮልፌዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ከሜዳቸው ነቅለው መውጣት የጠቀማቸው ጅማዎች አሁንም ተጨማሪ ጎል ለማግኘት እየተቃረቡ የመጡ ይመስል ነበር። በ61ኛው ደቂቃም ተመስገን ከርቀን የተሻገረውን የቅጣት ምት የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ተቆጣጥሮ መረብ ላይ ለማሳረፍ ቢጥርም ሀሳቡ ሳይሰምር ቀርቷል። 76ኛው ደቂቃ ላይ ግን ቡድኑ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሮ መሪነቱን አስፍቷል። በዚህም ተመስገን ከመሐል የተሰነጠቀለትን ኳስ ተከላካዮችን በልጦ በመሮጥ ግብ ጠባቂውን አልፎ ግብ አስቆጥሯል። ሁለተኛው ጎል ሲቆጠርባቸው የተረበሹት ኮልፌዎች በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ተናቦ መንቀሳቀስ ተስኗቸው ተቀይቷል።

ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ሊጠናቀቅ አምስት ደቂቃዎች ሲቀሩት ጅማዎች ሦስት ነጥባቸውን ከሦስት ጎል ጋር ይዘው የሚወጡበትን ጎል ከመረብ አሳርፈዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ተመስገን በሁለቱ የመሐል ተከላካዮች መካከል የተላከለትን ኳስ በጥሩ ሁኔታ ከመረብ ጋር አዋህዷል። በቀሪዎቹ ደቂቃዎችም ጨዋታው ተጨማሪ ጎል ሳያስተናግድ በጅማ አባጅፋር ሦስት ለምንም አሸናፊነት ፍፃሜውን አግኝቷል።

ውጤቱን ተከትሎ ተከታታይ ድል በማስመዝገብ ነጥቡን ሰባት ያደረሰው ጅማ አባጅፋር የቀሪ ተጋጣሚዎች ውጤት ሳይታወቅ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ከፍ ብሏል። በጨዋታው ሦስት ነጥብ ያስረከቡት ኮልፌዎች በበኩላቸው በስድስት ነጥቦች ወደ ወደ ሦስተኛ ደረጃ ሸርተት ብለዋል።