ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | መከላከያ ሰባት አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈረመ

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ጠንካራ ተፎካካሪ በመሆን ዓመቱን በሁለተኛ ደረጃነት ያጠናቀቀው መከላከያ ሰባት አዳዲስ ተጫዋቾችን በዛሬው ዕለት አስፈርሟል።

የመጀመሪያዋ ፈራሚ ዓባይነሽ ኤርቄሎ ሆናለች፡፡ ሀዋሳ ከተማን በተከላካይነት ከተቀላቀለች በኃላ በአንድ ጨዋታ በድንገት ግብ ጠባቂ በመሆን የተጫዋችነት ጉዞዋን የቀጠለችሁ ተጫዋቿ ሀዋሳ ከተማን ለአራት ዓመት ያገለገለች ሲሆን ለቀጣዩ የውድድር ዓመት ቆይታ ለማድረግ ወደ መከላከያ አምርታለች፡፡

በተመሳሳይ ከሀዋሳ ወደ መከላከያ ያመራችው አጥቂዋ መሳይ ተመስገን ነች፡፡ በሀዋሳ ከተማ ያለፉትን ሦስት አመታት በመጫወት ያሳለፈችው ተጫዋቿ ዘንድሮ በሴቶች ፕሪምየር ሊግ ለከፍተኛ ግብ አግቢነት ስትፎካከር ቆይታለች፡፡

ሌላኛዋ ከሀዋሳ ወደ መከላከያ ያቀናችው መቅደስ ማሞ ነች፡፡ ቁመተ ረጅሟ የመሐል አማካይ ከ2005 ጀምሮ በመሐል ወደ አዳማ ከማቅናቷ በስተቀር ረጅሙን የእግርኳስ ሕይወቷን ለሀዋሳ በአማካይ እና በአምበልነት በመጫወት ስታገለግል ቆይታለች፡፡

መከላከያ ከሀዋሳ ያስፈረመው አራተኛ ተጫዋች አማካይዋ ሳራ ኬዲ ነች። በአርባምንጭ ከተማ እግር ኳስን ከጀመረች በኋላ ያለፉትን አራት የውድድር ዓመታት በሀዋሳ አሳልፋ አሁን መዳረሻዋን ጦሩ አድርጋለች፡፡

ማዕድን ሳህሉም አዲሷ የክለቡ ፈራሚ ሆናለች፡፡ ዘንድሮ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን በተለይ በመጀመሪያው ዙር አስገራሚ አቋሟን ስታሳይ የነበረችው የቀድሞዋ የኢትዮጵያ ቡና እና ጥረት ኮርፖሬት አማካይ በድሬዳዋ ሁለት የውድድር ዓመትን በማሳለፍ ወደ ጦሩ አቅንታለች፡፡

የመጨረሻ ሁለት ፈራሚዎች የጌዲኦ ዲላዎቹ አማካይ ስመኝ ምኅረት እና እፀገነት ግርማ ናቸው፡፡ በዓመቱን ከጌዲኦ ዲላ ጋር ድንቅ እንቅስቃሴን ያደረጉት ተጫዋቾች መዳረሻቸው መከላከያ ሆኗል፡፡