አዳማ ከተማ ላይ ተላልፎ የነበረው ውሳኔ ፀንቷል

በቅርቡ በሦስት ተጫዋቾቹ ክስ የተመሰረተበት አዳማ ከተማ ያቀረበው የይግባኝ ጥያቄ ውድቅ በመሆን የተላለፈበት ውሳኔ ፀንቷል፡፡

በ2013 በኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ተሳታፊ ለሆነው አዳማ ከተማ ሲጫወቱ የነበሩ ቴዎድሮስ ላቀው፣ ፍሰሀ ቶማስ እና አካሉ አበራ በአዳማ ከተማ ውል እያላቸው በክለቡ መሰናባታቸው ይታወሳል፡፡ በክለቡም በመጋቢት ወር 2013 የ19 ወር ደመወዝ እያለን ያለ አግባብ ተሰናብተናል ያሉት ሦስቱ ተጫዋቾች ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን የቅሬታ ደብዳቤን ማስገባታቸው አይዘነጋም፡፡የተጫዋቾቹን የክስ ይዘት ሲከታተል የነበረው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን ኮሚቴም አዳማ ከተማ ተጫዋቾቹን ያለ አግባብ ነው ያሰናበተው ስለዚህ የተጫዋቾቹ ደመወዝ በሰባት ቀናት ውስጥ ተፈፃሚ እንዲሆን እንዲሁም ተጫዋቾቹን ወደ ስራ ገበታቸው እንዲመለሱ ይደረግ በማለት በደብዳቤ ለክለቡ አሳውቆ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ ተጫዋቾቹ በተባለው ሰባት ቀናት ውስጥ ውሳኔው ተግባራዊ ሊሆንልን አልቻለም በሚል በድጋሚ ቅሬታ ያቀረቡ ሲሆን አዳማ ከተማም ለይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ይግባኝ ማለቱ ይታወሳል፡፡ የፌዴሬሽኑ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴም በዛሬው ዕለት ባደረገው ስብሰባ አዳማ ከተማ ያቀረበው ይግባኝ አግባብ ባለመሆኑ በክለቡ ላይ የተላለፈው ውሳኔ እንዲፀና እና ተፈፃሚ እንዲሆን ክለቡም ለይግባኝ ያስያዘው ገንዘብም ለፌዴሬሽኑ ገቢ እንዲሆን ውሳኔ ተላልፏል፡፡

የውሳኔው ደብዳቤ 👇