አሴዴ የተባለው የስፔን ተቋም ለሀገራችን አሠልጣኞች የሰጠው ስልጠና ፍፃሜውን አግኝቷል

የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ የስፖርት አካዳሚ ከስፔኑ አሴዴ እና ኢትዮ ጋቫ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የአምስት ቀን የስልጠና ፕሮግራም ዛሬ ተጠናቋል።

ከሁለት ዓመታት በፊት ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር አብሮ ለመስራት ስምምነት ተፈራርሞ በእግርኳስ ፕሮጀክት ላይ የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ የሚገኘው የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ከ13 እና ከ15 ዓመት በታች ቡድኖችን እንዲሁም በቅርቡ ከ17 ዓመት በታች ቡድን በማዋቀር የእግርኳስ ልማት ስራዎችን እየከወነ እንደሚገኝ ይታወቃል። በአጠቃላይ 120 ታዳጊ ተጫዋቾችን (በወንድ 60 በሴት 60) በፕሮጀክት በማቀፍ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው የዩኒቨርስቲው የስፖርት አካዳሚ አሁን ደግሞ አሴዴ ከተባለው የስፔን ግብረሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር የስፖርት ልማት ወርክ ሾፕ አካሂዷል። የስፖርት አካዳሚው ከሦስት ወራት በፊት በጀመረው ግንኙነት የአሴዴ የስፖርት ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ሆኗል። ከባርሰሎና ከተማ የመጡት የአሴዴ አሠልጣኞችም የቅርጫት ኳስ እና የእግርኳስ ስልጠና ከሰኞ ጀምሮ በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ፔዳ ካምፓስ በሚገኘው ስታዲየም ለአምስት ተከታታይ ቀናት ሲሰጡ ነበር።

የስፖርት ትምህርት እና ስልጠና የሚሰጠው አሴዴ ከዩኒቨርስቲው ጋር የአምስት ዓመት የአብሮ የመስራት የውል ስምምነት የፈፀመ ሲሆን ሰኞ ዕለትም የመጀመሪያውን ዙር ስልጠና አስጀምሯል። በእግርኳሱ የተዘጋጀው ስልጠና የስፔን የእግርኳስ ሜቶዶሎጂ ምን እንደሆነ እና የእውቀት ሽግግር እንዲደረግ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል። በክፍል እና በመስክ በተሰጠው የእግርኳስ ስልጠና ላይም የኢትዮጵያ ፕሮፌሽናል ፉትቦለርስ አሶሴሽንን ወክለው ኤፍሬም ወንድወሰን፣ ፍቅሩ ተፈራ፣ አዳነ ግርማ እና ደረጄ መንግስቱ ተገኝተው ነበር። ከእነርሱ በተጨማሪ የፋሲል ከነማው ምክትል አሠልጣኝ ኃይሉ ነጋሽ የግብ ጠባቂዎች አሠልጣኝ አዳም ባዘዘው እንዲሁም የባህር ዳር ከተማ የሴቶች ቡድን ዋና አሠልጣኝ ሰርካዲስ እውነቱ በስፍራው ተገኝተው ስልጠናውን ሲወስዱ ታዝበናል።

በሁለቱ አካላት መካከል በተደረገው ስምምነት ላይ 80 በመቶ የሚሆነውን ድጋፍ ግብረሰናይ ድርጅቱ (አሴዴ) ሲችል ቀሪው 20 በመቶውን ደግሞ የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ እንደሚሸፍም የዩኒቨርስቲው የስፖርት አካዳሚ ዲን ዳኛቸው ንግሩ (ዶ/ር) አስረድተውናል። ከሚከናወነው የእውቀት ሽግግር በተጨማሪ አሴዴ ለአሠልጣኞችም ሆነ ለሰልጣኞች (በዩኒቨርሲቲው ስር ባሉ ፕሮጀክቶች የሚገኙ) የእግርኳስ ትጥቅ እና ቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ተጠቁሟል።

እግርኳስን ጨምሮ በሌሎቹም የስፖርት ዘርፎች ያለው የሙያ ስልጠና በአማራ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ለሚሰሩ የስፖርት ባለሙያዎች፣ ለፕሮጀክት ሰልጣኞች እንዲሁም ከክልል እና ፌዴራል ለተወጣጡ ስፖርተኞች የተዘጋጀ ነበር።

በቀጣይ ዩኒቨርስቲው በእግርኳስ፣ መረብ ኳስ፣ እጅ ኳስ፣ ቅርጫት ኳስ እና አትሌቲክስ ከፍ ባለ ደረጃ ለመስራት እቅድ እንዳለው ከአሴዴ ጋር በግላቸው ግንኙነት ፈጥረው ውጥኑን ያሳኩት ዳኛቸው ንግሩ (ዶ/ር) ገልፀውልናል። ከአሴዴ ጋር ባለው ስምምነት መሠረትም በየሦስት ወሩ ከስፔን ባርሰሎና የሚመጡ ባለሙያዎች እንደሚኖሩ ተጠቁሟል። ዶክተሩ አያይዘውም በቅርቡ ከኢትዮጵያ ሁለት ባለሙያዎች ወደ ስፔን ባርሰሎና በማምራት የስፔኖችን የእግርኳስ አደረጃጀት እና የስልጠና መንገድ አይተው እንደሚመጡ አውስተውናል።