ሀዋሳ ከተማ የአማካይ ስፍራ ተጫዋች አስፈረመ

በቃሉ ገነነ ሀዋሳ ከተማን የተቀላቀለ ሁለተኛ አዲስ ፈራሚ ተጫዋች ሆኗል፡፡

በአሰልጣኝ ዘርአይ ሙሉ እየተመራ ወደ ዝውውር ገበያው ጎራ ያለው ሀዋሳ ከተማ ከቀናቶች በፊት ተከላካዩ ፀጋሰው ድማሙን ከሀድያ ሆሳዕና ያስፈረመ ሲሆን በዛሬው ዕለት ደግሞ ሁለተኛ ፈራሚ በማድረግ አማካዩ በቃሉ ገነነን በሁለት ዓመት የውል ዕድሜ ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል፡፡ የቀድሞው የወልቂጤ ከተማ እና ስሑል ሽረ የአማካይ ስፍራ ተጫዋች የተጠናቀቀውን የውድድር አመት በአዳማ ከተማ ያሳለፈ ሲሆን ምንም እንኳን አዳማ ከተማ በፕሪምየር ሊጉ ውጤት ርቆት ቢዘልቅም ተጫዋቹ ግን ጥሩ የሜዳ ላይ ቆይታን ለክለቡ ማድረግ ችሏል፡፡ አዳማ ከተማ ዳግም ከወረደበት በማሟያ ጨዋታ ዳግም ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዲመለስ አስተዋጽኦን ማድረግ ችሎ የነበረው ተጫዋቹ በአዳማ ያሰለጠኑት ዘርዓይ ሙሉን እግር ተከትሎ ወደ ሀይቆቹ ቤት አምርቷል፡፡

ሀዋሳ ከተማ ከአዳዲስ ተጫዋቾች በተጨማሪ የዳንኤል ደርቤ፣ ኤፍሬም አሻሞ፣ ፀጋአብ ዮሐንስ፣ ተባረክ ኢፋሞ እና ምንተስኖት ጊንቦን ውል ማደሱም አይዘነጋም፡፡