የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰላለፍ ታውቋል

በሴካፋ ውድድር ሰባተኛ ደረጃን ይዞ ለማጠናቀቅ ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር የሚፋለመው የዋልያው የመጀመሪያ አሰላለፍ ታውቋል።

በሴካፋ ውድድር ሁለት የምድብ እና አንድ የደረጃ ጨዋታ አድርጎ ሦስት ነጥብ ማግኘት የተሳነው የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከሰዓታት በኋላ ሰባተኛ ደረጃን ለማግኘት እና ከድል ጋር ለመታረቅ ወደ ሜዳ ይገባል። አሠልጣኝ ውበቱ አባተም በኤርትራ አቻቸው ከተረቱበት የሰኞ ጨዋታ ሦሰት ለውጦችን በማድረግ ጨዋታውን እንደሚቀርቡ ታውቋል። በዚህም ረመዳን ናስር በዩሃንስ ሰጌቦ፣ ብሩክ በየነ በዱሬሳ ሹቢሳ እንዲሁም ወንድማገኝ ኃይሉ በዊልያም ሠለሞን ተተክተዋል።

በጨዋታው ፋሲል ገብረሚካኤል የቡድኑ የግብ ዘብ ሲሆን ዩሃንስ ሴጌቦ፣ መናፍ ዐወል፣ መሳይ ጻውሎስ እና አስራት ቱንጆ አራቱ ተከላካዮች ሆነዋል። አማካይ መስመር ላይ ከቅጣት የተመለሰው ዊልያም ሠለሞን ከዳዊት ተፈራ እና ከተከላካዮች ፊት ከሚቆመው በረከት ወልዴ ጋር የሦስትዮሽ ጥምረት ፈጥሯል። የቡድኑን የፊት መስመር ደግሞ ቸርነት ጉግሳ፣ አቡበከር ናስር እና ዱሬሳ ሹቢሳ እንደሚመሩት ተረጋግጧል።