ፈረሰኞቹ ከዩጋንዳዊ ግብ ጠባቂ ጋር ስማቸው ተያይዟል

ከቀናት በፊት ሰርቢያዊ አሠልጣኝ የሾሙት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በሴካፋ ውድድር ከታየው የግብ ዘብ ጋር ስማቸው በስፋት እየተያያዘ ይገኛል።

ስርቢያዊ ዝላትኮ ክራምፖቲችን ዋና አሠልጣኝ ከማድረጋቸው በፊት በዝውውር ገበያው ላይ ሲሳተፉ የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች አሠልጣኝ ካገኙ በኋላም ተጫዋች ወደ ስብስብ ለመቀላቀል እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኙ ሶከር ኢትዮጵያ ተረድታለች። ከዚህ ቀደም በረከት ወልዴ፣ ቸርነት ጉግሳ፣ ጋቶች ፓኖም፣ ቡልቻ ሹራ እና ምኞት ደበበን ያስፈረመው ክለቡ የግብ ዘቡ ቻርለስ ሉክዋጎን ወደ ስብስቡ ለመቀላቀል እየሰራ እንደሆነም የዩጋንዳ ብዙሃን-መገናኛዎች እየዘገቡ ይገኛሉ።

በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ባለው የሴካፋ ውድድር ላይ ከሀገሩ ጋር ሦስት ጨዋታዎችን ያደረገው ቻርለስ ሉክዋጎ ከዚህ ቀደም ለቪክቶሪያ ዩኒቨርስቲ፣ ፕሮላይን እና ሉዌዛ ግልጋሎት ሰጥቷል። ተጫዋቹ ከ2010 (2017) ጀምሮ ደግሞ ለኬሲሲኤ ሲጫወት የነበረ ቢሆንም የአንድ ዓመት ቀሪ ውል እያለው ከክለቡ ጋር በስምምነት መለያየቱ ተነግሯል።

ስዊፍት ስፖርት ዩጋንዳ የተሰኘው ድረ-ገፅ ባወጣው መረጃም በሴካፋ ውድድር ላይ ሀገሩን እያገለገለ የሚገኘው ሉክዋጎ የመዲናውን ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስን ሊቀላቀል እንደሆነ ያትታል።

ግብ ጠባቂው ዝውውሩን አጠናቆ ቅዱስ ጊዮርጊስን የሚቀላቀል ከሆነ ከዴኒስ ኦኒያንጎ፣ ካሊሲቡላ ሀኒንግተን እና ሮበርት ኦዶንካራ ቀጥሎ ፈረሰኞቹን የተቀላቀለ አራተኛው ዩጋንዳዊ ግብ ጠባቂ ይሆናል።