ወልቂጤ ከተማ የውጪ ዜጋ ጨምሮ ሦስት ተጫዋቾችን አስፈርሟል

በዝውውር መስኮቱ እንቅስቃሴ ሳያደርግ የቆየው ወልቂጤ ከተማ ሦስት አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈርሟል። የውጪ ተጫዋችም ከፈረሙት መካከል ይገኝበታል። 

ለቀጣዩ የውድድር ዓመት የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ ያደረገውና ይህን ተከትሎ በደጋፊዎች ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞ የገጠመው ክለቡ ከዚህ ቀደም የአሰልጣኙን ውል ማራዘም እና ከወጣት ቡድኑ ተጫዋቾች ለማሳደግ ላይ ብቻ ተገድቦ መቆየቱ የሚታወስ ነው። አሁን ደግሞ ለማስፈረም እንደተስማሙ ተገልፀው የነበሩ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ በመቀላቀል የዝውውር እንቅስቃሴውን ጀምሯል። በዚህም መሠረት ሰዒድ ሀብታሙ፣ ፋሲል አበባየሁ እና ጋናዊው ዋሀብ አዳምስ አዲስ ፈራሚዎች ሆነዋል።

የመጀመሪያው ፈራሚ ግብ ጠባቂው ሰዒድ ሀብታሙ ነው። የቀድሞው የጅማ አባ ጅፋር የግብ ዘብ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ወደ ወላይታ ድቻ አምርቶ ግማሽ ዓመት ከተጫወተ በኋላ ከክለቡ ጋር መለያየቱ የሚታወስ ሲሆን ሁለት ግብ ጠባቂዎችን ለለቀው ቡድኑ ጥሩ አማራጭ ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።

ሌላው ፈራሚ ፋሲል አበባየሁ ነው። የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ከዚህ ቀደም በ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የተጫወተ ሲሆን ያለፉትን የውድድር ዘመናት በከፍተኛ ሊጉ ክለብ ጌዲኦ ዲላ አሳልፏል።

ሦስተኛው ፈራሚ ጋናዊው ዋሀብ አዳምስ ነው። የመሐል ተከላካዩ በሀገሩ ክለቦች አዱዋና ስታርስ እና አሳንቲ ኮቶኮ የተጫወተ ሲሆን በቀጣዩ የውድድር ዘመን ለወልቂጤ ከተማ ለመጫወት ከስምምነት መድረሱ ታውቋል። ይህን ተከትሎ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ምንም የውጪ ተጫዋች ካልተጠቀሙ ክለቦች አንዱ የነበረው ወልቂጤ ከአንድ ዓመት በኋላ የውጪ ተጫዋች ወደመጠቀሙ የሚመለስ ይሆናል።