የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የእጣ ማውጣት ሥነ-ስርዓት የሚደረግበት ቀን ታውቋል

በ16 ክለቦች መካከል የሚደረገው የ2014 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የእጣ ማውጣት መርሐ-ግብር መቼ እንደሚወጣ ተገልጿል።

የሀገሪቱ ከፍተኛ የሊግ እርከን የሆነው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በቀጣይ የውድድር ዓመት በ16 ክለቦች መካከል እንደሚደረግ ይታወቃል። በውድድሩ የመሳተፍ ዕድል የነበራቸው ሦስቱ የትግራይ ክልል ክለቦች (መቐለ 70 እንደርታ፣ ወልዋሎ ዓ/ዩ እና ስሑል ሽረ) በተሰጣቸው ቀነ ገደብ ምዝገባ አለማከናወናቸውን ተከትሎም በሀዋሳው የማሟያ ውድድር ከአንድ እስከ ሦስት የወጡት አዳማ ከተማ፣ ወልቂጤ ከተማ እና ጅማ አባጅፋር ቦታውን እንደሚተኩ መረጋገጡ ይታወሳል።

ከማሟያ ውድድሩ በፊት በሊጉ መሰንበታቸው ያረጋገጡት አስሩ የሊጉ ክለቦች ለቀጣይ ዓመት ውድድር 200 ሺ ብር በመክፈል እስከ ሐምሌ 15 ድረስ ሲመዘገቡ ከከፍተኛ ሊግ ያደጉት አዲስ አበባ ከተማ፣ መከላከያ እና አርባምንጭ ከተማ ደግሞ የሚጠበቅባቸውን 300 ሺ ብር ከፍለው የውድድር ዓመቱን መጀመር እየተጠባበቁ ይገኛሉ። ከላይ የጠቀስናቸው እና በማሟያ ውድደሩ የትግራይ ክልል ክለቦችን የተኩት ደግሞ ከትናንት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ምዝገባ እንዲያከናውኑ ቢገለፅላቸውም ሦስቱም በትናንትናው ዕለት የሚጠበቅባቸውን 200 ሺ ብር በባንክ በማስገባት የአክሲዮን ማኅበሩ ቢሮ በመሄድ ምዝገባ እንዳከናወኑ ተረጋግጧል።

የክለቦች ምዝገባ በተገቢው ሁኔታ መጠናቀቁን ተከትሎ አክሲዮን ማኅበሩ የሊጉን የእጣ ማውጣት መርሐ-ግብር የፊታችን ሰኞ ሐምሌ 26 እንደሚያደርግ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች። ይህ የእጣ ማውጣት ሥነ-ስርዓትም 8:30 የክለብ ተወካዮች ባሉበት በአክሲዮን ማኅበሩ ጽሕፈት ቤት እንደሚከናወን ሲታወቅ ማኅበሩም ለተሳታፊ ክለቦች ከደቂቃዎች በፊት በደብዳቤ ጥሪ ማቅረቡን ተረድተናል።