ጀማል ጣሰው ወደ አዲስ ክለብ ለማምራት ተስማምቷል

የተጠናቀቀውን የውድድር ዓመት በወልቂጤ ከተማ ያሳለፈው ጀማል ጣሰው ወደ ሌላኛው የሊጉ ክለብ ለማምራት ስምምነት ላይ ደርሷል።

ከ1997 – 2000 በአሳዳጊ ክለቡ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከታችኛው እስከ ዋናው ቡድን ተጫውቶ ያሳለፈው ጀማል ከዛም ወደ ሀዋሳ፣ ደደቢት፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ መከላከያ፣ ጅማ አባ ቡና፣ ድሬዳዋ ከተማ እና ፋሲል ከነማ ተጉዞ የእግርኳስ ህይወቱን እንደቀጠለ ይታወቃል። በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን የወልቂጤ ከተማ አምበል የነበረው የግብ ዘቡም በቀጣይ ወደ አዳማ ከተማ ለመዘዋወር ከጫፍ መድረሱን ሶከር ኢትዮጵያ ተረድታለች።

አሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝን ከሾሙ በኋላ ፊታቸውን ወደ ተጫዋቾች ዝውውር በማዞር እንቅስቃሴ ላይ የሚገኙት አዳማዎች በዛሬው ዕለት ከተጫዋቹ ጋር የመጨረሻ ድርድር ማድረጋቸው ታውቋል። በነበረው ድርድርም ሁለቱም አካላት ስምምነት ላይ በመድረሳቸው የተጫዋቹ መዳረሻ አዳማ እንደሆነ እና አዲስ ነገር ካልተፈጠረ በስተቀር በቅርቡ ፊርማውን እንደሚያኖር ተገልጿል።