የቀጣይ ዓመት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር ዕጣ ወጥቷል

በጥቅምት ወር የመጀመሪያ ሳምንት እንደሚጀምር የሚጠበቀው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር የዕጣ ማውጣት መርሐ-ግብር ከሰዓታት በፊት ተከናውኗል።

ከ8:30 ጀምሮ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር አዲሱ ቢሮ በተከናወነው የዕጣ ማውጣት ሥነ-ስርዓት ላይ በውድድሩ የሚሳተፉ የክለብ ተወካዮች ተገኝተዋል። ከክለቦቹ በተጨማሪ ዕጣውን ከአክሲዮን ማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈ ጋር በመሆን የሚያወጣው ተጋባዡ እንግዳ አቡበከር ናስር ተገኝቷል። እጣው ከመውጣቱ በፊት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአክሲዮን ማኅበሩ የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ ከደቂቃዎች በኋላ በሚጀምረው የአትሌቲክስ ውድድር ላይ ኢትዮጵያ የተሻለ ውጤት እንዲገጥማት መልካም ምኞት ከተመኙ በኋላ ይህ የእጣ ማውጣት መርሐ-ግብር ሊጉ በክለቦቹ ከተያዘ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ እንደሚወጣ አውስተዋል። ሰብሳቢ አክለውም “ይህ የእጣ መውጣት ስነ-ስርዓት ክለቦች ባሉበት ሲወጣ የመጨረሻው ነው። ከዚህ በኋላ ግን አክሲዮን ማኅበሩ በራሱ አውጥቶ መረጃውን ይሰጣል።” ብለዋል። በመጨረሻም በቀጣዩ የውድድር ዓመት የተሻለ ነገር እንዲገጥም ምኞታቸውን ገልፀው አጭሩን ማብራሪያቸውን አገባደዋል።

ከሰብሳቢው የመክፈቻ ንግግር በኋላ የማኅበሩ ሥራ-አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሠይፈ እና የክብር እንግዳው አቡበከር ናስር እጣውን ማውጣት ጀምረዋል። በዚህም አቶ ክፍሌ የክለቦቹን ስም ከያዘውን ቋት እንዲሁም አቡበከር ተራ ቁጥር ከያዘውን ቋጥ በማውጣት የዓመቱ መርሐ-ግብር አሳውቀዋል። በመጀመሪያ ሳምንት የሊጉ መርሐ-ግብርም የሚከተሉት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

– አርባምንጭ ከተማ ከ መከላከያ

– ባህር ዳር ከተማ ከ አዲስ አበባ ከተማ

– ፋሲል ከነማ ከ ሀድያ ሆሳዕና

– አዳማ ከተማ ከ ወልቂጤ ከተማ

– ሀዋሳ ከተማ ከ ጅማ አባ ጅፋር

– ድሬዳዋ ከተማ ከ ወላይታ ድቻ

– ኢትዮጵያ ቡና ከ ሲዳማ ቡና

– ሰበታ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

እጣው ከወጣ በኋላ የውድድር እና ሥነ-ስርዓት ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት ወገኔ ዋልተንጉስ (ዶ/ር) የ2014 መርሐ-ግብር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ እና የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ወቅትን ታሳቢ እንደሚያደርግ አመላክተዋል። ዶ/ር ወገኔ አክለውም የመጨረሻው መርሐ-ግብር ማኅበራቸው በሚወስነው የውድድር ቅርፅ (ፎርማት) እና የስታዲየሞች ብዛት ከታወቀ በኋላ በብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች የቀን ለውጥ፣ በአፍሪካ ዋንጫ ላይ ብሔራዊ ቡድኑ ከውድድሩ አስቀድሞ ከተሰናበተ (ቡድኑ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰ በ5ኛ ቀኑ ይጀምራል)፣ ብሔራዊ ቡድኑ የ3ኛ ዙር የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጥሎ ማለፍ ውድድርን ካለፈ (ሊጉ ቢያንስ ለ19 ቀን ይቋረጣል) እንዲሁም አንድ ክለብ በአክሲዮን ማኅበሩ እውቅና ኢንተርናሽናል ውድድር ካለበት ለውጦች ሊኖሩ እንደሚችሉ አብራርተዋል።

ይህ ሥነ-ስርዓት ከተከናወነ በኋላ በስፍራው የተገኙ የብዙሃን መገናኛ አባላት እና የክለብ አመራሮች አዲሱን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ቢሮ እንዲጎበኙ ተደርጓል።