ካሣዬ አራጌ ለክለቡ ደብዳቤ አስገብቷል

የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች ለዝግጅት ቢሾፍቱ ቢደርሱም ዋና እና ረዳት አሠልጣኙ እስከ አሁን ድረስ ወደ ስፍራው አላቀኑም።

በዘንድሮ የውድድር ዘመን ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ የቀጣይ ዓመት የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ውድድር ተሳታፊ መሆኑን ያረጋገጠው ኢትዮጵያ ቡና በጳጉሜ ወር የሚጀመረውን የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ ተጠናክሮ ለመቅረብ በትናንትናው ዕለት ዝግጅቱን ለመጀመር ወደ ቢሾፍቱ አምርቷል። ሶከር ኢትዮጵያ ትናንት አመሻሽ ባስነበበችው ዘገባም የቡድኑ ተጫዋቾች ወደ ስፍራው ቢያቀኑም ዋና አሠልጣኙ ካሣዬ አራጌ እና ምክትል አሠልጣኙ ዘላለም ፀጋዬ እንዳልተጓዙ አትታ ነበር።

ዋና እና ምክትል አሠልጣኞቹ ወደ ስፍራው ያላመሩትም የአሠልጣኝ ዘላለም ውል ባለመታደሱ እንደሆነ ሲገለፅ ዋና አሠልጣኙም የረዳቱ ዘላለም ፀጋዬ ውል እንዲራዘም ፍላጎት እንዳለው ተሰምቷል። ይህንን ተከትሎም የምክትል አሠልጣኙን ውል ለማደስ ፍቃደኛ ያልሆነው ክለቡ አቋሙን እንዲለውጥ እና የረዳቱ ውል እንዲታደስለት አሠልጣኝ ካሳዬ አራጌ ደብዳቤ ማስገባታቸው ታውቋል። ነገሮችም በዚሁ የሚቀጥሉ ከሆነ ወደ ቢሾፍቱ ተጉዘው ቡድኑን ላይቀላቀሉ እንደሚችሉ እየተነገረ ይገኛል።

ይህንን ዘገባ እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ ክለቡ የምክትል አሠልጣኙን ውል ለማደስ ፍቃደኛ አለመሆኑን ተረድተናል። በአፍሪካ ውድድር ዝግጅት ዋዜማ ወደ መካረር እንዳያመራ የሚያሰጋው ይህ ጉዳይንም እየተከታተልን አዳዲስ ጉዳዮችን ይዘን የምንመጣ ይሆናል።