ፈረሰኞቹ አጥቂ ወደ ስብስባቸው ለመቀላቀል ንግግር ላይ ናቸው

ስርቢያዊውን ዝላትኮ ክራምፖቲች ዋና አሠልጣኝ አድርገው የሾሙት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ቶጎዋዊ አጥቂ የግላቸው ለማድረግ እንቅስቃሴ ላይ መሆናቸው ታውቋል።

ቀደም ብለው የበረከት ወልዴ፣ ቸርነት ጉግሳ፣ ጋቶች ፓኖም፣ ቡልቻ ሹራ እና ምኞት ደበበን ዝውውር የጨረሱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ዩጋንዳዊውን የግብ ዘብ ቻርለስ ሉክዋጎንም ለማስፈረም የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኙ ዘግበን ነበር። ሶከር ኢትዮጵያ አሁን ባገኘችው መረጃ ደግሞ ክለቡ ቶጎዋዊውን አጥቂ እስማኤል ኦሮ-አጎሮን ለማምጣት ንግግር መጀመሩን ያመላክታል።

የ25 ዓመቱ የመሐል አጥቂ ኦምኒስፖርትስ አጋዛ እና ኤ ኤስ ሲ ካራ ለተባሉ የሀገሩ ክለቦች ተጫውቶ ያሳለፈ ሲሆን ሀገሩ ቶጎንም ባሳለፍነው የቻን ውድድር አገልግሏል። 1 ሜትር ከ82 ሴንቲ ሜትር የሚረዝመው ተጫዋቹም መዳረሻው ኢትዮጵያ እንዲሆን ቅዱስ ጊዮርጊሶች ጠንከር ያለ ፍላጎት በማሳየት ንግግር እያከናወኑ እንደሆነ እና የቪዛ ፕሮሰስ መጀመራቸውን ተረድተናል።