ሲዳማ ቡና ረዳት አሰልጣኝ ሾሟል

በሲዳማ ቡና በተጫዋችነት እና ከ20 ዓመት በታች ቡድን አሰልጣኝነት ያገለገለው አሰልጣኝ የገብረመድኅን ረዳት ሆኖ ተሹሟል፡፡

በክረምቱ ከፍተኛ አንቅስቃሴ ያደረገውና ከሰሞኑ ተጨማሪ አዳዲስ ተጫዋቾች በተለይም ከሀገር ውጪ ለምጣት በሂደት ላይ የሚገኘው ሲዳማ ቡና በዛሬው ዕለት ወንድማገኝ ተሾመን ረዳት አሰልጣኝ አድርጎ ሾሟል፡፡ በግራ መስመር ተከላካይነት ለሲዳማ ቡና ፣ ሀዋሳ ከተማ ፣ ድሬዳዋ ከተማ ፣ ደቡብ ፖሊስ እና ሀድያ ሆሳዕና የተጫወተው ወንድማገኝ ተሾመ መጫወት ካቆመ በኋላ ያለፉትን ሁለት የውድድር ዘመናት የሲዳማ ቡናን ከ20 ዓመት በታች ቡድን በማሰልጠን ቆይቷል። አሁን ደግሞ የአሰልጣኝ ገብረመድኅን ረዳት ሆኖ እንዲሠራ የክለቡ ቦርድ በቦታው ሾሞታል፡፡

ሲዳማ ቡና በትናንትናው ዕለት ረፋድ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን በአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ መሪነት መከወን ጀምሯል፡፡