አሠልጣኝ አብርሃም መብራቱን ዋና አሠልጣኝ አድርገው የሾሙት ባህር ዳር ከተማዎች አዲስ ምክትል አሠልጣኝ ማግኘታቸው ታውቋል።
በቀጣዩ ዓመት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተጠናክሮ ለመቅረብ ከአሠልጣኝ ቅጥር ጀምሮ በርከት ያሉ አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ስብስባቸው ያመጡት ባህር ዳር ከተማዎች በዛሬው ዕለት የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን እንደሚጀምሩ ከቀናት በፊት ገልፀን ነበር። አሁን ድረ-ገፃችን ባገኘችው መረጃ ደግሞ የቀድሞ የክለቡ ተጫዋች ደረጄ መንግስቱ የአሠልጣኝ አብርሃም መብራቱ ምክትል ሆኖ ብቅ ማለቱን ይጠቁማል።
በሙገር ሲሚንቶ፣ ሀረር ቢራ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ዳሽን ቢራ የተጫዋችነት ጊዜውን አሳልፎ የጣናው ሞገዶቹን የተቀላቀለው ደረጄ ቡድኑን በአምበልነት እየመራ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ማሳደጉ ይታወሳል። ደረጄ በተጫዋችነት ቀሪ የአንድ ዓመት ውል ቢኖረውም አሁን በምክትል አሠልጣኝነት ሚና አዲስ ሀላፊነት ማግኘቱ ታውቋል።
ከደረጄ በተጨማሪ አሠልጣኝ አብርሃም መላኩ እና የግብ ጠባቂዎች አሠልጣኝ አሻግሬ በአዲሱ የአሠልጣኝ ቡድን ውስጥ እንደሚቀጥሉ ሲታወቅ የፋሲል ተካልኝ ምክትል የነበረው ታደሠ ግን ከምክትል አሠልጣኝነቱ መነሳቱ ተመላክቷል።