የመዲናው ክለብ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን የሚጀምርበት ቀን ታውቋል

አዲሱ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ክለብ አዲስ አበባ ከተማ እጅግ ዘግይቶ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ሊጀምር ነው።

በአሠልጣኝ እስማኤል አቡበከር እየተመራ የሀገሪቱን ከፍተኛ የሊግ እርከን ዳግም የተቀላቀለው አዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ የውስጥ አሰራሮች ምክንያት በዝውውር ገበያው ላይ በንቃት ሳይሳተፍ ቀርቶ ነበር። ባለፉት ጥቂት ቀናት ግን ክለቡ የውስጥ ግምገማውን በማገባደድ ለቀጣዩ ዓመት የሊጉ ውድድር መዘጋጀት ጀምሯል። በዚህም የመቀጠላቸው እና አለመቀጠላቸው ጉዳይ በእንጥልጥል የቆየውን አሠልጣኝ እስማኤል ጉዳይ ውሳኔ በመስጠት የነባር ተጫዋቾቹን ውል ማደስ ጀምሯል።

በርከት ያሉ አዳዲስ ተጫዋቾችን ለማስፈረም በእንቅስቃሴ ላይ የሚገኘው ክለቡም ከዛሬ ከሰዓት ጀምሮ አብረውት የሚቀጥሉት ነባር ተጫዋች እንዲሰባሰቡ ጥሪ አስተላልፎ ነበር። ተጫዋቾቹ አራት ኪሎ አካባቢ በሚገኘው ወወክማ እንዲሰባሰቡ የተደረገ ሲሆን ከነገ ጀምሮ የህክምና ምርመራ እንደሚያደርጉ ተጠቁሟል። ተጫዋቾቹ ማረፊያቸውን ባደረጉበት ቦታ በግላቸው ልምምድ እየሰሩ ከቆዩ በኋላ ደግሞ ከአዲስ ዐመት በኋላ ወደ ሀዋሳ እንደሚጓዙ እና መደበኛ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን ከመስከረም 3 ጀምሮ እንደሚቀጥሉ ታውቋል።