የዋልያዎቹ አሠልጣኝ እና አምበል ከነገው ጨዋታ በፊት መግለጫ ሰጥተዋል

👉”በጋናው ጨዋታ በመሸነፋችን ተጫዋቾቹም ሆነ የአሠልጣኝ ቡድን አባላቱ ቅር ተሰኝተናል” ውበቱ አባተ

👉”በተክለማርያም ምክንያት አይደለም የተሸነፍነው። በጨዋታው የተሸነፍነው ጎል ማግባት ስላልቻልን ነው” ውበቱ አባተ

👉”ተጫዋቾቹ በጥሩ የራስ መተማመን ላይ ነው የሚገኙት” ጌታነህ ከበደ

👉”ነገ የሜዳችን ጨዋታ ስለሆነ አሸንፈን ለመውጣት የማጥቃት ሀይላችንን አሻሽለን እንገባለን” ውበቱ አባተ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ከነገው የዚምባቡዌ ጨዋታ በፊት የቅድመ ጨዋታ አስተያየት ከቡድኑ አምበል ጌታነህ ከበደ ጋር በመሆን ሰጥተዋል። ብሔራዊ ቡድኑ ባረፈበት ብሉ ናይል (አቫንቲ) ሆቴል በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይም ዋና አሠልጣኙ የጋናውን ጨዋታ አስመልክቶ በቅድሚያ ገለፃ አድርገዋል።

“የጋናውን ጨዋታ ብዙ ሰው እንደተከታተለው አስባለሁ። ጋና ለእኛ ትልቅ ተጋጣሚ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ከቡድኑ ጋር ከሜዳችን ውጪ በደጋፊዎች ፊት ነው የተጫወትነው። በተቻለን መጠን ባቀድነው መንገድ ለመጫወት ሞክረናል። በዚህም ጨዋታውን እስከ መጨረሻው ለመቆጣጠር ሞክረን ባሰብነው መንገድ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ደቂቃ ድረስ ለመጫወት ችለናል። እውነት ለመናገር ተጫዋቾቹ ባሳዩት ነገር ደስተኛ ነኝ። ከከባድ ተጋጣሚ ጋር ቢያንስ ነጥብ ተጋርቶ ለመውጣት መጣራችን እና በጨዋታው ያሳየነው እንቅስቃሴ በጣም ጥሩ ነው። ቡድናችንም በጨዋታው ጥሩ የግብ ዕድሎችን ሲፈጥር ነበር። ግን እንደ ክፍተት በርከት ያሉ ዕድሎችን አለመፍጠራችን እና በራሳችን ሜዳ ላይ ያለንን መረጋጋት በተጋጣሚም ሜዳ አለማሳየታችን ነው። እንደ አጠቃላይ በጋናው ጨዋታ በመሸነፋችን ተጫዋቾቹም ሆነ የአሠልጣኝ ቡድን አባላቱ ቅር ተሰኝተናል። ቢያንስ አቻ መውጣት ነበረብን። ዓርብ ያሳየነው እንቅስቃሴ ትልቅ ምዕራፍ ነው። ከዚህ ቀደም ከምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ጋራ ስንጫወት የነበረብንን ጫና መቀነስ የቻለ እንቅስቃሴ ነው። በአጠቃላይ በጨዋታው ከመሸነፋችን ውጪ የታየው ነገር ጥሩ ነው። ደስተኞችም ነን። በጨዋታውም የተቆጠረብን ጎል በቀላሉ የሚያዝ ነበር። ይህ ደግሞ በእግርኳስ የሚያጋጥም ነገር ነው።” ብለዋል።

አሠልጣኝ ውበቱ አባተ አያይዘው በጨዋታው በግብ ዘቡ ተክለማርያም ሻንቆ ስህተት የተፈጠረውን ጎል አስመልክቶ ተከታዩን ብለዋል።

“በእግርኳስ ጨዋታዎች ከእጅህ የሚያመልጡበት የተለያዩ ምክንያቶች አሉ። በዓርቡም ጨዋታ እኛ ላይ ያ አጋጣሚ ተፈጠረ። በእግርኳስ ደግሞ እንደዛ አይነት አጋጣሚዎች ይፈጠራሉ። በተለያዩ ውድድሮች የሚፈጠሩ ስለሆነም እንዴት፣ በምን እና በማን እያልን አጋጣሚው ላይ አልቆዘምንም። ትልቁ ነገር ጋናን ሜዳቸው ድረስ ተጉዘን ገጥመን ያሳየነው ብቃት ነው። ከዚህ ቀደም ያለንን ታሪክ እናውቃለን። በተክለማርያም ምክንያት አይደለም የተሸነፍነው። በጨዋታው የተሸነፍነው ጎል ማግባት ስላልቻልን ነው። ስለዚህ አሁን ግብ ማስቆጠር የምንችልበትን ዕድል ነው መፍጠር የሚጠበቅብን እንጂ ያቺን ስህተት እያስታወስን መቆዘም የለብንም። ግብ ጠባቂውን የቀየርነውም ለራሱም ሆነ ለቡድኑ ጥቅም ስንል እና ከዛ በኋላ የሚፈጠረውን ችግር ለመቀነስ ነው። ምንም እንኳን በግብ ጠባቂ ስህተት ብንሸነፍም ያ አጋጣሚ በ90 ደቂቃ የሚፈጠር ቅፅበት ነው።”

ከአሠልጣኙ በመቀጠል መድረኩን የያዘው የቡድኑ አምበል ጌታነህ ከበደ በበኩሉ አሠልጣኙ የዓርቡን ጨዋታ በተመለከተ የሰጡትን ሀሳብ በተከታዩ ንግግሩ አጠናክሯል።

“አፍሪካ ውስጥ ጋና ትልቅ ቡድን ነው። በጨዋታው ቡድናችንን በደንብ አይተንበታል። ከጋና ስንመለስ ውጤተቱ አይገባንም ብለን ነው የመጣነው። ከዚህ ቀደም ከጋና ጋር ስንጫወት እንደዚህ አይነት ነገር አልነበረም። በርከት ያሉ ግቦችን እንደምናስተናግድ ወይም ተሸንፈን እንደምንመጣ አውቀን ነበር ጨዋታውን የምንቀርበው። አሁን ግን ተቆጭተን ነው የመጣነው።” ብሏል።

ከተጫዋቻቸው በመቀጠል በድጋሜ ንግግር ማድረግ የቀጠሉት አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ምድቡን በተመለከተ “አሁን ያለንበት ምድብ ክፍት እንደሆነ እና እስከ መጨረሻው ድረስ መቀጠል እንደምንችል ይሰማኛል። አሁን ላይ ይሄ ቡድን ነው ተጠባቂ ብሎ መናገር የሚከብድ ይመስለኛል።” ካሉ በኋላ ቡድናቸው እድገት እያሳየ እንደሆነ ጠቁመው በነገው ጨዋታ ያላቸውን አቀራተብ አውስተው ሀሳባቸውን አገባደዋል።

“ሁሌ እንደምለው ከዛምቢያው የወዳጅነት ጨዋታ ጀምሮ ቡድናችን እየተሻሻለ ነው የመጣው። በጋናው ጨዋታ ላይ የተሻሻለው ሌላኛው ነገር በመከላከል አወቃቀር የነበረው ነገር ነው። ይህ ትልቅ መሻሻል ነው። ነገ የሜዳችን ጨዋታ ስለሆነ አሸንፈን ለመውጣት የማጣቃት ሀይላችንን አሻሽለን እንገባለን። አቀራረባችንም በዚህ መልክ ነው የሚሆነው።”

በመጨረሻም የቡድኑ አምበል ጌታነህ ከበደ የነገውን ጨዋታ በተመለከተ ተከታዩን ሀሳብ ሰጥቷል።

“ተጫዋቾቹ በጥሩ የራስ መተማመን ላይ ነው የሚገኙት። በሜዳችንም እንደመጫወታችን ያለንን የሜዳላ ላይ የአሸናፊነት መንፈስ እንጠቀምበታለን። እንደተመለከታችሁት በጋናውም ጨዋታ ጥሩ ተንቀሳቅሰናል። ነገም በተመሳሳይ በጥሩ ሁኔታ ጨዋታውን እንቀርባለን።”