የኢትዮጵያ እና ዚምባብዌ ብሔራዊ ቡድኖች የመጨረሻ ልምምዳቸውን ሰርተዋል

በነገው ዕለት በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ ሁለተኛ ጨዋታ የሚያደርጉት የኢትዮጵያ እና ዚምባቡዌ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ከጨዋታው በፊት የመጨረሻ ልምምዳቸውን አከናውነዋል።

ኳታር ለምታስተናግደው የ2022 የዓለም ዋንጫ ለማለፍ የምድብ የማጣሪያ ጨዋታዎችን ከደቡብ አፍሪካ፣ ዚምባቡዌ እና ጋና ጋር ተደልድሎ እያከናወነ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሦስት ቀናት በፊት ወደ ጋና አምርቶ አንድ ለምንም ተሸንፎ ወደ ሀገሩ መመለሱ ይታወቃል። በምድቡ የሚገኘው ሌላኛው ቡድን ዚምባቡዌ ደግሞ በተመሳሳይ ቀን በሜዳው ደቡብ አፍሪካን አስተናግዶ ያለ ግብ አቻ ተለያይቶ ነበር። ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖችም በነገው ዕለት ሁለተኛ የምድብ ጨዋታቸውን በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ለማከናወን በዝግጅት ላይ ይገኛሉ።

በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከወሳኙ የነገው ጨዋታ በፊት ዛሬ ረፋድ የመጨረሻ ልምምዱን አከናውኗል። ብሔራዊ ቡድኑም ከረፋዱ አምስት ሰዓት ጀምሮ በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ቀለል ያለ ልምምድ ሰርቷል። በስብስቡ ውስጥ የሚገኙት ሀያ ሦስቱም ተጫዋቾች በተሳተፉበት የልምምድ መርሐ-ግብር ላይ አሠልጣኙ ከኳስ ጋር የተገናኙ ሥራዎችን ሲያሰሩ ነበር። ሶከር ኢትዮጵያ ከብሔራዊ ቡድኑ ባገኘችው መረጃም ሁሉም ተጫዋቾች በመልካም ጤንነት ላይ ይገኛሉ።

ለዚህ ጨዋታ ቅዳሜ ምሽት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በትናንትናው ዕለት ባህር ዳር የገቡት ዚምባቡዌዎች በበኩላቸው ማረፊያቸውን በዲላኖ ሆቴል እንዳደረጉ ለማወቅ ተችሏል። ስብስቡ ትናንት 10 ሰዓት በዋናው ስታዲየም በሚገኘው የመለማመጃ ሜዳ የመጀመሪያ ልምምዱን ካደረገ በኋላ በዛሬው ዕለት ጨዋታውን በሚያከናውንበት ስታዲየም ለአንድ ሰዓት ከአስራ አምስት ደቂቃዎች የቆየ የመጨረሻ ልምምዱን አከናውኗል።

የሁለቱ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኞች ከጨዋታው በፊት የሰጡትን መግለጫ ደግሞ ከቆይታ በኋላ ይዘን የምንቀርብ ይሆናል።