ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና ከአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ጨዋታዎች ውጪ ሆኗል

የዩጋንዳውን ዩ አር ኤ በመልስ ጨዋታ ባህርዳር ኢንተርናሽናል ስታዲየም ላይ የገጠመው ኢትዮጵያ ቡና 3-1 በሆነ ውጤት ተሸንፏል።

ኢትዮጵያ ቡናዎች ዩጋንዳ ላይ ከተደረገው ጨዋታ አቡበከር ናስር እና ሚኪያስ መኮንን በሥዩም ተስፋዬ እና አላዛር ሽመልስ በመለወጥ ነበር ጨዋታውን የጀመሩት።

ቀዳሚው አጋማሽ ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ ጀምሮ የኢትዮጵያ ቡናዎች የኳስ ቁጥጥር እየጎላበት የሄደ ነበር። 14ኛው ደቂቃ ላይ በአበበ ጥላሁን ኢላማውን የጠበቀ ቅጣት ምት ሙከራ ማድረግ የጀመሩት ቡናዎች በአመዛኙ በተጋጣሚ ሜዳ ላይ ኳስ ይዘው ተንቀሳቅሰዋል። በተቃራኑው ዩ አር ኤዎች ከኳስ ውጪ የቡናን ተጫዋቾች እንቅስቃሴ በመቆጣጠር በመልሶ ማጥቃት ወደ ፊት ለመሄድ ሲሞክሩ ታይተዋል። በዚህ ሂደት የጨዋታው ቀጣይ ከባድ ሙከራ በቡና በኩል ሲታይ 22ኛው ደቂቃ ላይ የቡድኑ ቅብብሎች በዩ አር ኤ የግራ ሳጥን ገብተው አስራት ቱንጆ ከታፈሰ ሰለሞን የደረሰውን ኳስ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ቢሞክርም ወደ ላይ ተነስቶበታል።


ቀጣዮቹ ደቂቃዎች እንግዶቹ ባሰቡት መንገድ ወደ ግብ መድረስ የቻሉባቸውን አጋጣሚዎች አሳይተውናል። 26ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን እንዲሁም 33ኛው ደቂቃ ላይ ኦጄራ ጆኪያም ከቀኝ መስመር ያሻማው ኳስ በክሮምዌል ሩቶሚዮ በግንባር ተገጭተው ለጥቂት ወጥተዋል። ከሁለተኛው የሩቶሚዮ ሙከራ ሦስት ደቂቃዎች በኋላ የዩ አር ኤ ሳጥን አቅራቢያ ከአስራት የተቀበለውን ኳስ እንዳለ ደባልቄ ወደ ግብ መትቶ የግቡ ቋሚ መልሶበታል። አጋማሹ ሊጠናቀቅ አራት ደቂቃዎች ሲቀሩት ግን የዩጋንዳዊያኑ ቀጥተኛ አጨዋወት ሰምሮላቸው ሩቶሚዮ ከመሀል የደረሰውን ኳስ ሞክሮ በአቤል ማሞ ቢመለስበትም በድጋሚ በማስቆጠር ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል።

ሁለተኛው አጋማሽ ላይ የአብቃል ዓሉሙን በአላዘር ዘለቀ በመለወጥ እና ሽግሽጎችን በማድረግ የጀመሩት ቡናዎች ይበልጥ ለማጥቃት ገፍተው ወደ ዩጋንዳዊያኑ ሜዳ በመቅረብ ቅብብሎቻቸውን እየከወኑ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረዋል። ይሁን እንጂ ይህ ሁኔታ ለዩ አር ኤዎች የተመቸ ሆኖ በመልሶ ማጥቃት ሁለት ተከታታይ ግቦችን አስቆጥረዋል። 52ኛው ደቂቃ ላይ ቡድኑ በቀኝ በኩል ከፈጠረው ድንገተኛ ጫና ማንዴላ አሽራፍ ከጠባብ አንግል መትቶ ሲያስቆጥር ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ አምበሉ ካጊሙ ሻፊክ ከዚሁ መስመር የደረሰውን ኳስ በቀላሉ ከመረብ ማሳረፍ ችሏል።

ከዚህ በኋላ ዩ አር ኤዎች ሙሉ ለሙሉ በራሳቸው የግብ ክልል ላይ መቆየትን መርጠዋል። በአንፃሩ ቡናዎች በተጋጣሚያቸው ዙሪያ ባላቸው ኃይል ሁሉ ከፍተቶችን ለማግኘት ጥረዋል። በዚህም ሂደት ውስጥ እንዳለ ደባልቄ ላይ በተሰራ ጥፋት አስራት ቱንጆ 70ኛው ደቂቃ ላይ ልዩነቱን ያጠበበትን የፍፁም ቅጣት ምት ጎል አስቆጥሯል።


በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ቡናዎች በተመሳሳይ ሁኔታ ግብ ለምግኘት ቢሞክሩም ዩጋንዳዊያኑ በቂ ክፍተት አልስጧቸውም። እነርሱም አልፎ አልፎ በመልሶ ማጥቃት ለመውጣት ያደርጉት ጥረት ቢታይም ተጨማሪ ግብ የሚያስገኝላቸው አልሆነም። በቡና በኩል አማንኤል ዮሐንስ 72ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ጠርዝ ላይ ያደረገው ሙከራ በቀላሉ በግብ ጠባቂው ሲያዝ በጭማሪ ደቂቃ እንዳለ ደባልቄ በአየር ላይ የላከለትን ኳስ አቤል እንዳለ ከቅርብ ርቀት ለማግባት ያደረገው ጥረት ሳይሳካ ጨዋታው ተፈፅሟል።

በዚህም መሰረት ዩ አር ኤ በድምር ውጤት 5-2 በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፏል።