በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ተጋባዡ ክለብ እንደማይሳተፍ ታውቋል

የደቡብ ሱዳኑ ክለብ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ እንደማይሳተፍ ሲታወቅ በምትኩ አንድ የፕሪምየር ሊግ ክለብ መግባቱ ተረጋግጧል።

በሁለት ምድብ ተከፍሎ ከመስከረም 15-30 ድረስ በሚካሄደው የመዲናዋ ትልቅ ውድድር ላይ በተጋባዥነት እንደሚካፈል በፌዴሬሽኑ በኩል ማረጋገጫ ተሰጥቶት የቆየው ሙኑኪ ኤፍ ሲ በምድብ ሀ መደልደሉ ይታወሳል። አሁን ባገኘነው መረጃ መሠረት በአዲስ አበባ በሚኖረው ቆይታ ለሆቴል እና ለሌሎች ጉዳዮች የሚወጣው ወጪ ከፍተኛ በመሆኑ እና ከፌዴሬሽኑ አቅም በላይ ስለሆነ በሚል በምትኩ አንድ ቡድን እንዲገባ መደረጉን ሰምተናል።

በዚህም መሠረት በአሠልጣኝ አሸናፊ በቀለ የሚመራው ጅማ አባ ጅፋር ለአስራ አምስተኛ ጊዜ በሚካሄደው የመዲናዋ ዋንጫ ላይ ተሳታፊ መሆኑን አዘጋጅ ኮሚቴው አረጋግጦልናል። ጅማ አባ ጅፋር በምድብ ሀ ከኢትዮጵያ ቡና አዲስ አበባ ከተማ እና መከላከያ ጋር የሚደለደል ይሆናል።

የፊታችን ቅዳሜ መስከርም 15 ቀን በሚጀምረው የከተማው ዋንጫ መርሐግብሩ እንደ ደረሰን እናሳውቃለን።