ድሬዳዋ ከተማ ጋናዊ ተከላካይ አስፈረመ

የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን በሀዋሳ ከተማ እየሰራ የሚገኘው ድሬዳዋ ከተማ ጋናዊ የመሐል ተከላካይ በዛሬው ዕለት አስፈርሟል።

በርከት ያሉ አዳዲስ ተጫዋቾችን በማስፈረም ከነባር ተጫዋቾች ጋር በማቀናጀት በሀዋሳ ከተማ በታደሰ እንጆሪ ሆቴል ማረፊያቸውን በማድረግ የቅድመ ውድድር ዝግጅት መስራት ከጀመሩ የሰነባበቱት ድሬዳዋ ከተማዎች በዛሬው ዕለት ጋናዊውን የመሀል ተከላካይ አውዱ ናፊዩን በአንድ አመት ውል አስፈርመዋል።

ለሀገሩ ክለቦች ቤርኩም ቼልሲ ፣ አሻንቲ ጎልድ እና አሻንቲ ኮቶኮ በመጫወት የክለብ ህይወቱን የቀጠለው ተከላካዩ ያለፉትን ሦስት ዓመታት አሻንቲ ኮቶኮን ከለቀቀ በኋላ በኢኳቶሪያል ጊኒው ክለብ ፉትሮስ ኪንግ በመጫወት ካሳለፈ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በዛሬው ዕለት ብርቱካናማዎቹን ተቀላቅሏል፡፡

ድሬዳዋ ከተማ ከሰሞኑም ለበርካታ ተጫዋቾች የሙከራ ዕድልን እየሰጠ የሚገኝ ሲሆን በሙከራው ጥሩ ብቃት ማሳየት የሚችሉ አዳዲስ ተጫዋቾችን ያስፈርማል ተብሎም ይጠበቃል፡፡