የክለቦች የውድድር ዘመን ቅድመ ዳሰሳ | ሰበታ ከተማ

የሊጉ ክለቦች ዝግጅት እና የመጪው ውድድር ዘመን ምልከታችን ወደ ሰበታ ከተማ ይወስደናል።


ሰበታ ከተማ ከስምንት ዓመታት ቆይታ በኋላ ወደ ሀገሪቱ ትልቁ ሊግ ከተመለሰ ወዲህ ሦስተኛ የውድድር ዓመቱን ይጀምራል። አምና ሁለተኛ በነበረው ዓመቱ በ37 ነጥቦች አምስተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ክለቡ ዘንድሮ ደግሞ ወደ ዋንጫው ፉክክር ይበልጥ መጠጋትን ያልማል። በተለይም በሁለተኛው ዙር የነበረውን አካሄድ ማስቀጠል ከውጤት አንፃር ለዘንድሮው ህልሙ መነሻ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ከወራጅ ቀጠናው በአስተማማኝነት ያላረቀውን የአንደኝ ዙር ጉዞውን በአንድ ሽንፈት ብቻ በጨረሰባቸው የሁለተኛው ዙር ጨዋታዎች ነበር የተስተካከሉት። ከአጠቃላዩ 37 ነጥቦችም 23ቱ በዚሁ ዙር የተሰበሰቡ ነበሩ። ክለቡ ከውጤት አንፃር ጥሩ ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል ዓመትን ቢያሳልፍም ከሜዳ ውጪ የነበሩ ከደመወዝ ክፍያ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ስሙ ሲነሳ ማሳለፉ አይዘነጋም። ከቀናት በኋላ በሚጀምረው የዘንድሮው ውድድር ላይ እንደቡድን በብዙው ተለውጦ የሚቀርበው ሰበታ የመሻሻል ውጥኑ ከውጤት አንፃር ብቻ ሳይሆን ከፋይናንስ እና አስተዳደር ጉዳዮችም አኳያ እንደሚሆንም ይጠበቃል።

ሰበታ በ2014 በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ በስብስብ እና በአጨዋወት መንገዳቸው ፍፁም ተለውጠው ሊቀርቡ ከሚችሉ ክለቦች መካከል ይጠቀሳል። ለውጡ ደግሞ ከአሰልጣኝ ቅጥርም ይጀምራል። ወደ ሊጉ ከተመለሰ በኋላ በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ እና አብርሀም መብራቱ ሰልጥኖ ያለፈው ክለቡ አሁን ደግሞ አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራውን ወደ ኃላፊነት አምጥቷል። አምና ሁለተኛውን አጋማሽ የውድድር ጊዜ በወላይታ ድቻ አስደናቂ መነቃቃትን ያሳየ ቡድን ያስመለከቱን አሰልጣኙ በአዲሱ ክለባቸው ለቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት አብረው ለመዝለቅ ተስማምተዋል። አሰልጣኝ ዳንኤል ገብረማርያም እና አሰልጣኝ ብርሀን ደበሌ ደግሞ ሰበታ በምክትልነት የሾማቸው ረዳቶች ሆነዋል። በተጨማሪም xiያሱ ደስታ የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ ፣ ቢኒያም ተፈራ የህክምና ባለሙያ እንዲሁም ጥላሁን ነጋሽ የቡድን መሪ በመሆን ክለቡን ያገለግላሉ።

ሰበታ ከተማዎች አምና ከተጠቀሙባቸው ተጫዋቾች ውስጥ ከ13 በላይ ከሚሆኑት ጋር ተለያይተዋል። አሰልጣኝ አብርሀም በዋነኝነት ይጠቀሙባቸው ከነበሩ ዋና ዋና ተጫዋቾች ውስጥ ፋሲል ገብረሚካኤል፣ ዳዊት እስጢፋኖስ፣ መስዑድ መሐመድ፣ ቡልቻ ሹራ ፣ ፉዐድ ፈረጃ እና ኦሴ ማውሊን መሰል ተጫዋቾች ከክለቡ ጋር አብረው አለመቀጠላቸው በገበያው ላይ በስፋት እንደሚሳተፍ ፍንጭ የሚሰጥ ነበር። በመሆኑም ክለቡ ለዓለም ብርሃኑን በግብ ጠባቂነት በረከት ሳሙኤል፣ ወልደአማኑኤል ጌቱ እና ታፈሰ ሰርካን ተከላካይ መስመር ላይ በኃይሉ ግርማ፣ አክሊሉ ዋለልኝ፣ ዘላለም ኢሳይያስ እና ፍፁም ተፈሪ በአማካይ ክፍሉ እንዲሁም ጁኒያስ ናንጄቦ፣ ሳሙኤል ሳሊሶ፣ መሐመድ አበራ፣ ዘካሪያስ ፍቅሬ እና ዮናስ አቡሌን በአጥቂነት ቦታ አምጥቷል። ከዝውውሮቹ ባሻገር ደግሞ ባሳለፍነው ዓመት ከነበረው ስብስብ ውስጥ የፍፁም ገብረማርያም እና ዱሬሳ ሹቢሳ ውል ተራዝሟል።

ሰበታ ከተማ ከዋናው ቡድን ቀጥሎ ያሉ የወጣት ቡድኖችን ያልያዘ በመሆኑ በዘንድሮው ስብስብ ውስጥ አዳዲስ ፊቶችን ማሳየት ቀላል አልሆነለትም። ቡድኑ ዝግጅቱን በሚያደርግበት ወቅትም በርከት ያሉ ታዳጊዎች አብረው የመሥራትን ዕድል አግኝተዋል። ከወጣቶቹ ውስጥ ክለቡ ላሰባቸው የዕድሜ ዕርከን ቡድኖች እንዲሁም ለዋናው ቡድን የሚሆኑትን የመለየት ሥራ ሲሰራ ቆይቷል። በዚህም አስቻለው ታደሰ፣ አንተነህ ናደው እና ሀምዛ አብዱልመናን በልዩ አረንጓዴ መታወቂያ የተመዘገቡ ተጫዋቾች ሆነዋል።


የሰበታ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅት ዕቅድ በቦታ ረገድ በአስገዳጅ ሁኔታዎች የተቀየረ ነበር። ከክለቡ ልምድ በመነሳት አዳማ ላይ ለመዘጋጀት ቢታሰብም በውድድር እና የብሔራዊ ቡድን ዝግጅት ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል። ወንጂ በከፍተኛ ዝናብ፣ ቢሾፍቱ በሚዘጋጁ ክለቦች መብዛት፣ ባቱ በታዳጊዎች ሻምፒዮና ምክንያት ከክለቡ ምርጫ ውጪ ሆነው በመጨረሻ ሀዋሳ የክለቡ የክርምት መቀመጫ ሆናለች። ሰበታዎች ከነሀሴ 14 ጀምረው በከተማዋ ባሉት የሰው ሰራሽ ፣ የግብርና እና በዋናው ስታድየም ጎን በሚገኝ ሜዳ ከሌሎች ክልቦች መርሐ ግብር ጋር በመናበብ ልምምዳቸውን ሲሰሩ ቆይተዋል።

የቡድኑ የዝግጅት ጊዜ በአራቱ ንዑስ የሥልጠና ክፍሎች ቴክቲክ ፣ ቴክኒክ ፣ በአካል ብቃት እና ሥነ ልቦናን ያካለለ እንደነበር አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ይናገራሉ። የልምምድ ጊዜው ዋና ግብ የነበረው ደግሞ ነባሮችን ከአዲሶቹ ጋር አዋህዶ የቡድን መግባባቱን ሥራ በጥሩ ጅምር ላይ እንዲከወን ማድረግ ላይ ነበር። ሰበታ በርካታ አዳዲስ ተጫዋቾችን ማስፈረሙ እና በአዲስ አሰልጣኝ መመራቱ ሲታይ በዚህ ነጥብ ላይ አመዛኙን ጊዜ ማሳለፉ የሚያስገርም አይሆንም። ስብስቡ ይህንን ፈተና በቶሎ በመወጣት በሚፈለገው የውህደት ደረጃ ላይ እንዲደርስ የሚያግዘው በቡድኑ ውስጥ ያለው ልምድ መሆኑ የአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ዕምነት ነው። “ካመጣናቸው ተጫዋቾች ከሦስት የማያንሱ በነበሩበት ክለቦች አምበል ሆነው ሲሰሩ የነበሩ ተጫዋቾች ናቸው። ከመከላከያ አራት ተጫዋቾች አምጥተናል። በእርግጥ መከላከያ ከፍተኛ ሊግ ነበር። ነገር ግን አስቀድሞ በፕሪምየር ሊጉ ሲጫወቱ የነበሩ ተጫዋቾች ናቸው። አሁን አዲስ የፈረሙት ተጫዋቾች ዕቅዳችንን ከማሳካት አንፃር በቂ ናቸው።”


እንደሚታወሰው በ2013ቱ ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጥቂት የማይባሉ ክለቦች ከደመወዝ ክፍያ ጋር በተያያዘ ከተጫዋቾቻቸው ጋር ለውዝግብ ሲዳረጉ ተስተውሏል። የዚህ ችግር ተጠቂ የነበረው ሰበታ ከተማም ተጨዋቾቹ ልምምድ እስከማቆም የደረሱበት ጊዜ እንደነበር አይዘነጋም። ይህ ጉዳይ በክለቦች ዘንድ እየተለመደ መምጣቱ “ሰበታ ዘንድሮም በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ያልፍ ይሆን ?” የሚል ስጋትን ይጭራል። ነገር ግን አሰልጣኝ ዘላለም በዚህ ጉዳይ ላይ ቆምጨጭ ያለ አቋም ይዘዋል። አሰልጣኙ እስካሁን ያለው ነገር ጥሩ ቢሆንም በቀጣይ ችግሮች ፈፅሞ አይኖርም ብሎ ማሰብ እንሰማይቻል ያምናሉ። ነገር ግን የልምምድ ማቆም እና መሰል ሁኔታዎች በበድናቸው ውስጥ ፈፅሞ እንደማይፈጥር አስረግጠው ተናግረዋል። ችግሮች ቢኖሩ እንኳን ትክክለኛው አግባብ እየሰሩ ጥያቄ ማቅረብ ብቻ እንደሆነ በፅኑ እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

በሰበታ ከተማ ውስጥ የሚጠበቀው ሌላኛው ለውጥ የአጨዋወት ምርጫን ይመለከታል። ክለቡ በሊጉ ባለፉት ሁለት የውድድር ዓመታት አብሯቸው ከሰራው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ እና አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ የሥልጠና መንገድ አንፃር ለኳስ ቁጥጥር ከፍተኛ ቦታ ነበረው። ለዚህም አጨዋወት የሚሆኑ እና ልምዱ ያላቸው ተጫዋቾችን ይዞ የነበረ በመሆኑ በአመዛኙ ግቦችን ከኋላ ተመስረተው ከሚመጡ ቅብብሎች ለማግኘት ሲጥር ይታይ ነበር። በአንፃሩ አሁን ኃላፊነቱን የያዙት አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ጠንካራ የመከላከል መሰረት ያላቸው ቀጥተኝነትን በቀላቀለ አጨዋወት ወደ ግብ ለመድረስ የሚሞክሩ ቡድኖችን በመስራት ይታወቃሉ። በተለይም አምና በወላይታ ድቻ በግማሽ የውድድር ዓመት ካሳዩት አንፃር የተጋጣሚን አጨዋወት መሰረት ያደረገ ተለዋዋጭ አቀራረብ ያለው ቡድን እንሰሚያሳዩን ይጠበቃል።

ከዓመቱ የሊግ ፉክክር በፊት በክረምቱ የሚደረጉ የዝግጅት ውድድሮች ሙሉ ለሙሉ የቡድኖችን ውጤታማነት እና አጨዋወት ይናገራሉ ባይባልም የሚሰጡት ፍንጭ ግን ይኖራል። በዚህ ረገድ ሰበታ ከተማ በተሳተፈበት የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ላይ አራት ጨዋታዎችን አድርጎ በሦስት ድል እና በአንድ ሽንፈት አሸናፊ መሆን ችሏል። በውድድሩ ከአሸናፊነት ባለፈ ጥሩ የመግባባት ደረጃ ላይ እንዳለ የሚጠቁም ጊዜን አሳልፏል። በግልም ነጥረው ሊወጡ የሚችሉ ተጫዋቾች ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድም ይችላል።

በዚህ ረገድ ናሚቢያዊው አጥቂ ጁኒያስ ናንጄቦ አንዱ ነው። በድሬዳዋ ከተማ የአምና ቆይታው ብዙ ጥረት ሲያደርግ እና ለቡድን አጨዋወት የተመቸ ሆኖ ቢታይም በግብ ፊት የነበሩት ውሳኔዎቹ ደካማ ነበሩ። በዝግጅት ውድድሩ ወቅት ሦስት ግቦች ማስቆጠሩ እና ከቡድኑ ጋር በፍጥነት ተዋህዶ መታየቱ ግን ዘንድሮ እንዲጠበቅ ያደርገዋል። ቡድኑ ተለዋዋጭነትን መርሁ ካደረገም ንናንጄቦ ለቀጥተኛ አጨዋወት ጥሩ አማራጭን ይፈጥራል። ሌላው ከዚህ ቀደም በአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ስር በመከላከያ ተጫውቶ ያለፈው መሀመድ አበራ ነው። እንደ ናንጄቦ ሁሉ በሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ተስፋን ያሳየው አጥቁው ከጉዳት ነፃ ሆኖ በቂ የመጫወት ዕድል ካገኘ ምናልባትም የሊጉ ክስተት ሊሆን ይችላል።

በአምናው ስብስብ ውስጥ ተቀይሮ በመግባት የሚታዩ ተፅዕኖችን ሲፈጥር የነበረው ዱሬሳ ሹቢሳ በአዲሱ አሰልጣኝ ስር ጥቅም ላይ ሲውል መመልከታችንም ተጫዋቹ የተሻለ ዕድገት የሚያስመዘግብበት ዓመት ከፊቱ ሊጠብቀው እንደሚችል ያመለክታል። በኢትዮ ኤሌክትሪክ የመሀል ተከላካይ ቦታ ላይ የምናውቀው ወልደአማኑኤል ጌቱም ወደ ፕሪምየር ሊጉ ባደረግው ምልሰት በቦታው ካሉ ተፎካካሪዎቹ የተሻለ የመሰለፍ ዕድልን ካሳካ የዓይን ማረፊያ የመሆን ዕድል አለው።

ሰበታ ከተማ ጥቅምት 10 ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስን በመግጠም ዓመቱን ይጀምራል።

የሰበታ ከተማ የ2014 ስብስብ

ግብ ጠባቂዎች

1 ምንተስኖት አሎ
22 ለአለም ብርሀኑ
29 ሰለሞን ደምሴ
55 ቶማስ ትግስቱ (U-23)

ተከላካዮች

4 አንተነህ ተስፋዬ
5 ጌቱ ኃይለማርያም
6 ወልደአማኑኤል ጌቱ
12 ቢያድግልኝ ኤልያስ
13 ታፈሰ ሰርካ
14 ዓለማየሁ ሙለታ
15 በረከት ሳሙኤል
19 ዮናስ አቡሌ
23 ኃይለሚካኤል አደፍርስ
አስቻለው ሁንዴ (U-23)
ሀብታሙ ጉልላት (U-23)

አማካዮች

2 ፍጹም ተፈሪ
18 አብዱልሀፊዝ ቶፊክ
21 በኃይሉ ግርማ
26 አክሊሉ ዋለልኝ
27 ክሪዚስቶም ንታምቢ
30 ዘላለም ኢሳይያስ
አንተነህ ናደው (U-23)
ሀምዛ አብዱልመናን (U-23)
የሀሳቡን ልንገረው (U-23)
ነገሰ ገመቹ (U-23)
ረጂብ ናስር (U-23)
ናኦል አካሉ (U-23)
ቦዳ አዴቻ (U-23)

አጥቂዎች

7 ዱሬሳ ሹቢሳ
9 ሳሙኤል ሳሊሶ
10 ዘካሪያስ ፍቅሬ
11 መሐመድ አበራ
16 ፍጹም ገብረማሪያም
20 ጁንያስ ናንጄቦ