ሪፖርት | በመክፈቻው ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ ባለድል ሆኗል

የመስፍን ታፈሰ ብቸኛ ግብ ሀዋሳ ከተማ ጅማ አባ ጅፋርን 1-0 በማሸነፍ ዓመቱን እንዲጀምር አድርጋለች።

በጨዋታው ጅማሮ ሀዋሳ ከተማዎች በተሻለ ሁኔታ ጫና ሲፈጥሩ ታይተዋል። የመጀመሪያውን ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ 4ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ ኤፍሬም አሻሞ ከረቀት ወደ ግብ የላከውን ኳስ ዮሃንስ በዛብህ በቀላሉ ይዞበታል። በቃሉ ገነነም እንዲሁ ከርቀት ሌላ ሙከራ አድርጎ ወደ ውጪ ወጥቶበታል። የሀዋሳዎችን ፈጣን የማጥቃት ሽግግር በማብረድ ጅማ አባ ጅፋሮች የጨዋታውን ሚዛን ወደ ራሳቸው ለማምጣት ጥረት ማድረግ በጀመሩባቸው ቀጣይ ደቂቃዎች ግብ አስተናግደዋል።

15ኛው ደቂቃ ላይ ጅማዎች ከሜዳቸው በቅብብል ለመውጣት ያደረጉትን ጥረት የቋረጡት ሀዋሳዎች በብሩክ በየነ እና ወንድምአገስኝ ኃይሉ ቅንጅት የፈጠሩትን የመጨረሻ ዕድል መስፍን ታፈሰ ወደ ግብነት ተቀይሯል። ግጭቶች እየተበራከቱ በሄዱባቸው የአጋማሹ ቀሪ ደቂቃዎች ጅማዎች ተወስዶባቸው የነበረውን ብልጫ ቀልብሰው ታይተዋል።

በ20ኛው ደቂቃ የዳዊት ፍቃዱ የመልሶ ማጥቃት ሙከራ ወደ ግብ መድረስ የጀመሩት ጅማዎች ቀጥተኝነት ይነበባቸው ነበር። ቀስ በቀስ ግን ኳስ ወደ መያዙ እያመዘኑ ሄደው የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫን ማግኘት ችለዋል። ከአዳማ የመስመር አጥቂነት ጊዜው በኋላ በመሀል ተከላካይነት የተመለከትነው በላይ አባይነህ ኢላማውን የጠበቀ የቅጣት ምት ሙከራ በመቀጠል የቡድኑ እጅግ የሚያስቆጨው ሙከራ የታየው 39ኛው ደቂቃ ላይ ታይቷል። የዳዊት እስጢፋኖስ እና መሀመድኑር ናስር አንድ ሁለት ቅብብል ከቅርብ ርቀት በመሀመድኑር አማካይነት ወደ ግብነት ሊቀየር ቢቃረብም የሀዋሳው ግብ ጠባቂ ዳግም ተፈራ በድንቅ ብቃት አድኖበታል።


ወደ ማብቂያው ላይ መስዑድ መሀመድን በተስፋዬ መላኩ ለውጠው በማስገባት በተመሳሳይ ሁኔታ የቁጥጥር ብልጫ ይዘው የቀጠሉት ጅማዎች አቻ ሳይሆኑ ጨዋታው ወደ ዕረፍት አምርቷል።


ሁለተኛው አጋማሽ በእንቅስቃሴ ደከም ያለ ሆኗል። በአመዛኙ መሀል ሜዳ ላይ ቆይቶ የታየው የቡድኖቹ ፍልሚያ ከቆሙ እና ከመስመር ከሚላኩ ካሶች መነሻነት አልፎ አልፎ የግብ ዕድሎች ሲፈጠሩበት ቢታዩም እንደመጀመሪያው የጠሩ እና ግብ ጠባቂዎችን የሚፈትኑ አልነበሩም። ይህንን ለማረምም ይመስላል በሀዋሳ በኩል ተባረክ ሄፋሞ በጅማ በኩል ደግሞ ቤካም አብደላ እና ዱላ ሙላቱን የመሳሰሉ የመስመር አጥቂዎች ወደ ሜዳ ገብተው ነበር።

ሜዳ ላይ የሚታየው እንቅስቃሴ ዓይን መሳብ እየተሳነው ጨዋታው 80 ደቂቃን ሲያልፍ ተቀይሮ በመውጣት በተጠባባቂዎች ወንበር ላይ የነበረው ዳዊት እስጢፋኖስ ኳስ አቀባይ ላይ የውሀ ፕላስቲክ ጠርሙስ ወርውርሀል በሚል የቀይ ካርድ ሰለባ መሆን ትኩረት ሳቢ ሆኗል። ጨዋታው ወደ ፍፃሜው ሲቀርብ አቻ ለመሆን ጥረት ላይ የነበሩት ጅማዎች ረዘም ያሉ ኳሶችን ወደ ፊት በመላክ የግብ ዕድል ለመፍጠር ሲጥሩ ሀዋሳዎች ይበልጥ የመልሶ ማጥቃት ቅፅበቶችን ለመፍጠር ሞክረዋል። ያም ቢሆን ሌላ ግብ ሳንመለከት ጨዋታው በሀዋሳ ከተማ 1-0 መሪነት ተጠናቋል።