ቅድመ ዳሰሳ | ወላይታ ድቻ ከ ሀዋሳ ከተማ

የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ሁለተኛ ጨዋታን እንዲህ ቃኝተነዋል።

በአሠልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም የሚመራው ወላይታ ድቻ በመጀመሪያ ሳምንት የሊጉ መርሐ-ግብር ለድሬዳዋ ከተማ ሦስት ነጥብ ማስረከቡ ይታወሳል። በጨዋታው ቡድኑ እስከ መጨረሻው ደቂቃ ወደ ሜዳ ይዞት የገባውን አንድ ነጥብ ይዞ የሚወጣ ቢመስልም የሄኖክ አየለ የመጨረሻ ደቂቃ ጎል ሽንፈት እንዲገጥመው አድርጎታል። ነገም ቡድኑ የመጀመሪያ ድሉን በማግኘት በቶሎ የአሸናፊነት መስመሩን ለመያዝ እና የዓምና የአጀማመር ችግሩም ለመቅረፍ እንደሚታትር ይታሰባል።

አዲስ አበባም ሆነ ሀዋሳ ላይ በተደረጉት የቅድመ ውድድር ጨዋታዎች ላይ ያልተሳተፈው ድቻ የቡድን ውህደት ችግር እንዳለበት በድሬው ጨዋታ በግልፅ ታይቷል። ይህ ክፍተት ደግሞ ከዝግጅት ጨዋታዎች እጥረት እንደሆነ ይታመናል። አሠልጣኙም ”ቅንጅት ይቀረናል” ማለታቸው ችግሩ በቶሎ መፍትሔ ላይኖረው እንደሚችል እና ለነገውም ጨዋታ እንቅፋት ሊሆን እንደሚችል ይገመታል። ከዚህ ውጪ ግን የቡድኑ ተጫዋቾች ላይ የሚታየው የትኩረት ማነስ ችግር በወሳኝ የሜዳ ክፍሎች ላይ ተከስቶ ዋጋ እንዳያስከፍል ያሰጋል።

በመስመር ላይ ያመዘነ የማጥቃት አጨዋወት በመጀመሪያው ጨዋታ ሲከተል የታየው ቡድኑ በነገውም ጨዋታ ተመሳሳይ የማጥቃት ሀሳብ እንደሚኖረው ይታሰባል። በተለይ በምንይሉ ወንድሙ ላይ ያነጣጠረ ግብ የማግኛ ሀሳብ እንደሚኖረውም ዕሙን ነው። ከዚህ ውጪ ግን በድሬዳዋው ጨዋታ ቡድኑ አዘውትሮ ሲከተለው የነበረው የቆሙ ኳሶች ነገም ሊቀጥሉ እንደሚችሉ ይታሰባል። ፊት ላይ የሚታየው የአጨራረስ ክፍተት እና የመጨረሻ የቅብብሎች ስኬት መውረድ ከተቀረፈ ደግሞ ለሀዋሳ ከባድ ተጋጣሚ መሆኑ አይቀርም።

ድቻዎች በነገው ጨዋታ በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም። ዋነኛ አጥቂያቸው ስንታየሁ መንግሥቱም በጥሩ ሁኔታ እያገገመ መሆኑ እና ለነገው ጨዋታ ዝግጁ መሆኑ ደግሞ ለቡድኑ መልካም ዜና ነው።

በአዲስ አሠልጣኝ ዘንድሮ ብቅ ያለው ሌላኛው ክለብ ደግሞ ሀዋሳ ከተማ ነው። አሠልጣኝ ዘርዓይ ሙሉን በመሾም ለውድድር የቀረበው ክለቡም በሊጉ የመክፈቻ ጨዋታ ድል አስመዝግቦ አጀማመሩን አሳምሯል። ነገም ይህንን የአሸናፊነት መንገድ ለማስቀጠል እና በደረጃ ሠንጠረዡ አናት ለመዝለቅ ድቻን ማሸነፍ ይጠበቅበታል።

ፈጣን እና ቀጥተኛ አጨዋወት ሲከተሉ የታዩት ሀዋሳዎች ነገም በተመሳሳይ ባህሪ ሊቀርቡ ይችላሉ። በተለይ ኳሶችን ከተጋጣሚ አቋርጦ በቶሎ ወደ ማጥቃት በማሸጋገር አደጋን የመፍጠር ከፍተኛ አጨዋወታቸው ነገ ለወላይታ ድቻዎች ፈተናን ይዞ ብቅ ሊል ይችላል። ከምንም በላይ ደግሞ ፈጣኖቹ ብሩክ፣ መስፍን እና ኤፍሬም የሚኖራቸው ከኳስ ጋር እና ከኳስ ውጪ መታተር እንዲሁም አፈትላኪ ሩጫዎች በጎ ነገር ለቡድኑ ይዞ ሊመጣ እንደሚችል ይታመናል። ከዚህ ውጪ መስመር ላይ ያመዘኑ ጥቃቶችም እንደሚኖሩ ከመጀመሪያው ጨዋታ መነሻነት መናገር ይቻላል።

ሀዋሳ በሦስትም ሆነ በአራትም ተከላካይ መጫወት መቻሉ ተጋማች እንዳይሆን እንደሚያግዘው ይታመናል። እንደ ደካማ ጎን ግን በጅማው ጨዋታ ከግቡ በኋላ ብዙውን ደቂቃ ጨዋታው ላይ የጎላ ተፅዕኖ ሳያሳድሩ መቆየታቸው እና በወጥነት አለመዝለቃቸው መነሳት ያለበት ነጥብ ነው። በተለይ ተጋጣሚ ኳስ ሲይዝባቸው የመደበቅ ባህሪ ማሳየታቸው እና እንደ አጀማመራቸው አለመዝለቃቸው ጥያቄን የሚያስነሳ ጉዳይ ሆኗል።

እንደ ወላይታ ድቻ ሁሉ ሀዋሳም ቤት ምንም የተረጋገጠ የጉዳት እና የቅጣት ዜና የለም። ነገርግን የመስመር ተጫዋቹ ዳንኤል ደርቤ የመሰለፉ ጉዳይ አጠራጣሪ ነው ተብሏል። ከዚህ ውጪ ጋናዊው የግብ ዘብ መሐመድ ሙንታሪ ከስራ ፍቃድ ጋር ተያይዞ ከነገው ፍልሚያ ሙሉ ለሙሉ ውጪ ነው።

12 ሰዓት የሚደረገውን የሁለቱን ቡድኖች ጨዋታ ደግሞ ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው እንደሚመሩት ታውቋል።

ግምታዊ አሠላለፍ

ወላይታ ድቻ (4-3-3)

ጽዮን መርዕድ

በረከት ወልደዮሐንስ – አንተነህ ጉግሳ – ደጉ ደበበ – አናጋው ባደግ

ሀብታሙ ንጉሤ – ንጋቱ ገብረሥላሴ – እድሪስ ሰዒድ

ምንይሉ ወንድሙ – ስንታየሁ መንግሥቱ- ቃልኪዳን ዘላለም

ሀዋሳ ከተማ (3-4-3)

ዳግም ተፈራ

አዲስ ዓለም ተስፋዬ – ላውረንስ ላርቴ – ፀጋሰው ድማሙ

መድሃኔ ብርሃኔ – አቡዱልባሲጥ ከማል – ወንድማገኝ ኃይሉ – በቃሉ ገነነ

ኤፍሬም አሻሞ – ብሩክ በየነ – መስፍን ታፈሰ