ሪፖርት | ወልቂጤ እና አርባምንጭ አቻ ተለያይተዋል

በወልቂጤ ከተማ እና አርባምንጭ ከተማ መካከል የተደረገው የምሽቱም ጨዋታ ያለግብ ተጠናቋል።

አራት ተጠባባቂዎችን ብቻ በመያዝ ጨዋታውን የጀመረው ወልቂጤ ከተማ በፋይናንስ ችግር ምክንያት ልምምድ ያቆሙ በርካታ ተጫዋቾቹን ባለመጠቀሙ ለዮናታን ፍሰሀ ፣ አበባው ቡታቆ ፣ ፋሲል አበባየሁ ፣ ፍፁም ግርማ እና አላዛር ዘውዴ የቀዳሚ ተሰላፊነት ዕድል ሰጥቷል። አርባምንጭ ከተማዎች በበኩላቸው ከፋሲል ጋር ነጥብ በተጋሩበት ጨዋታ ግብ ጠባቂው ሳምሶን አሰፋን በይስሀቅ ተገኝ ፣ በቀይ ካርድ ያጡት አሸናፊ ፊዳን በማርቲን ኦኮሮ ፣ መላኩ ኤሊያስን በሙና በቀለ እንዲሁም ጉዳት የገጠመው ፀጋዬ አበራን በሱራፌል ዳንኤል ተክተዋል።


ጨዋታው ለሀገር መከላከያ ሰራዊት የሞራል ድጋፍ በመስጠት የተጀመረ ነበር። ከጅምሩ ከባድ ሙከራ ሲያሳየን ሁለተኛው ደቂቃ ላይ የሀቢብ ከማል ድንቅ ቅጣት ምት በሲልቪያን ግቦሆ ተመጣጣኝ ብቃት ግብ ከመሆን ድኗል። ወልቂጤዎች ኳስ ተቆጣጥረው መሀል ለመሀል ለማጥቃት በሞከሩባቸው ቀዳሚ ደቂቃዎች በአርባምንጭ ሜዳ ሲቆዩ ታይተዋል። በአንፃሩ አርባምንጬች የሜዳውን ስፋት በተሻለ ሁኔታ በመጥቀም ፈጣን ጥቃቶችን ለመሰንዘር ሞክረዋል። 13ኛው ደቂቃ ላይ የወልቂጤዎችን ኳስ ምስረታ ከሳጥኑ ብዙም ሳይርቅ ባቋረጡበት ቅፅበት በላይ ገዛኸኝ ሀቢብ ያበረደለትን ኳስ ከሳጥን ውስጥ ከቀኝ አቅጣጫ አክርሮ ሞክሮ በግቦሆ የተመለሰበት ሙከራም ለግብ የቀረበ ነበር።


በሂደት የመልሶ ማጥቃት ባህሪ እየተላበሱ የታዩት ወልቂጤዎች ኳስ በተጋጣሚ በሚያዝባቸው አጋጣሚዎች በመታተር ክፍተቶችን እየዘጉ ኳስ ሲነጥቁ በፍጥነት ወደ ሳጥን የማድረስ ምልክት አሳይተው ነበር።18ኛው ደቂቃ ላይ ጌታነህ ከበደ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታው ኳስ የቡድኑ ቀዳሚ ሙከራ ሆኖ ሲታይ በግብ ጠባቂው ይስሀቅ ተገኝ ተይዟል።

ከውሀ ዕረፍቱ በኋላ ተመጣጣኝ ፉክክር ሲያስመለክተን የነበረው ጨዋታ የኃይል ሚዛን ወደ ወልቂጤ አድልቷል። በፈጠሩት ጫናም ተደጋጋሚ የቆመ ኳስ ዕድሎችን ሲያገኙ 36ኛው ደቂቃ አበባው ቡታቆ በቀኝ ካደላ ቅጣት ምት ጥሩ ሙከራ አድርጎ ግብ ጠባቂው አድኖበታል። በጥሩ ፍልሚያ የቀጠለው ጨዋታ ንኪዎች እየበረከቱበት ሄዶ ቡድኖቹን ወደ አስገዳጅ ቅያሪዎች ወስደዋቸዋል። በተለይም ወልቂጤዎች የተሟላ ተጠባባቂ የሌላቸው በመሆኑ ያለተፈጥሯዊ የመሀል ተከላካይ ጨዋታውን ለመቀጠል ተገደዋል።


ሁለተኛው አጋማሽ በጥሩ የፉክክር መንፈስ ሲጀምር 49ኛው ደቂቃ ላይ ከወልቂጤዎች በተቀማ ኳስ በላይ ገዛኸኝ በጥሩ ሁኔታ ያሳለፈውን ኳስ ኤሪክ ካፓይቶን ቀይሮ የገባው ፍቃዱ መኮንን ሳጥን ውስጥ በመግባት አክርሮ ቢሞክርም የግቡ ብረት መልሶበታል። ሆኖም አጋማሹ በጀመረበት መንፈስ አልቀጠለም። በሁለቱም በኩል የማጥቃት ፍላጎት ቢኖርም እንቅስቃሴዎቻቸው የተቆራረጡ ነበሩ።

ቀጣዩ የጨዋታው ትኩረት የሚስብ አጋጣሚ የተፈጠረው 66ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። እንዳልካቸው መስፍን ሳጥን ውስጥ ከኳስ ጋር ተገኝቶ በአበባው ቡታቆ ጥፋት ተሰርቶበታል የሚለው የአርባምንጮች ጥያቄ በኢንተርናሽናል አርቢትር ቴዌድሮስ ምትኩ ተቀባይነት አላገኘም። በሁኔታው ብዙ የተከራከሩት አርባምንጮች ሁለት የቢጫ ካርዶች ተመዞባቸዋል።


በአጋማሹ በሁለት አጋጣሚዎች በጌታነህ ከበደ አማካይነት የሳጥን ውጪ ሙከራዎች ያደረጉት ወልቂጤዎች በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ወደ ግብ ለመድረስ የሚያደርጉት ጥረት በተደጋጋሚ ይታይ ነበር። ጨዋታው የተለየ መነቃቃት ሳያሳይ ወደ መጨረሻው ሲቃረብ የተሻለ ጫና የፈጠሩት አዞዎቹም ሆኑ ሰራተኞቹ አብዝተው የፈለጉትን ጎል ማግኘት ሳይችሉ እንደአጀማመሩ ያልዘለቀው ፍልሚያ ፍፃሜውን አግኝቷል።


የአቻ ውጤቱን ተከትሎ አርባምንጭ አምስተኛ ወልቂጤ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ረግተዋል።