በባህር ዳር ቅሬታ ዙሪያ ምላሽ ተሰጥቷል

የዳኞች ኮሚቴ በፌደራል ዳኛ ቢኒያም ወርቅአገኘሁ ውሳኔ ላይ የተነሳውን ቅሬታ ተመልክቷል።

ቀደም ሲል ባቀረብነው ዘገባ ላይ ባህር ዳር ከተማ በትናንትናው ዕለት ከፋሲል ከነማ ጋር በነበረው ጨዋታ ማብቂያ ላይ ‘በረከት ደስታ ሁለተኛ ቢጫ ካርድ ተሰጥቶት ጨዋታውን እንዲጨርስ ተደርጓል’ በሚል ለሊግ ካምፓኒው የቅሬታ ደብዳቤ ማስገባቱን ገልፀን ነበር። የዚህን ቅሬታ ጉዳይ የተመለከተ ስብስባ የተቀመጠው የዳኞች ኮሚቴ ያሳለፈውን ውሳኔም ከኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ልዑልሰገድ በጋሻው ለማጣራት ሞክረናል።

አቶ ልዑልሰገድ እንዳሉትም ኮሚቴው በዋነኝነት የዋና ዳኛውን እና የዕለቱን ኮሚሽነር ሪፖርት እንደተመለከተ እና በሁለቱም ሪፖርቶች ላይ ተጫዋች በረከት ደስታ አንድ ቢጫ ካርድ ብቻ እንደተመለከተ መመዝገቡን ገልፀዋል። ባህር ዳር ከተማ በደብዳቤው ላይ በውሳኔው መዛነፍ ዙሪያ የተንቀሳቃሽ ምስል ማቅረብ የሚችል መሆኑን አስመልክተውም ኮሚቴው ውሳኔዎቹን የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን እንደተመለከተ ነግረውናል።

ሆኖም በሜዳ ላይ ውሳኔዎች ሲሰጡ የዳኞች አካላዊ አገላለፅ እንደሁኔታ ሊለያይ እንደሚችል አብራርተዋል። አርቢትሮች በውሳኔያቸው የአካላዊ እንቅስቃሴ ስህተት ቢሰሩ እንኳን እዛው አርመው የመመዝገብ ሥልጣኑ እንዳላቸውም ጨምረው ተናግረዋል። በመሆኑም ኮሚቴው ከላይ በተቀመጡት ነጥቦች ላይ ተመስርቶ የክለቡን ቅሬታ ውድቅ ማድረጉን ገልፀውልናል።