ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ | የ 17ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ውሎ

ዛሬ በተጠናቀቀው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 17ኛ ሣምንት ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ልደታ ክ/ከ ድል ሲቀናቸው ተጠባቂው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የአርባምንጭ ከተማ ጨዋታ አቻ ተጠናቋል።አዲስ አበባ ከተማ 0-1 ኢትዮ ኤሌክትሪክ

ረፋድ ላይ በተደረገው የዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሕይወት ዳንጊሶ ብቸኛ የፍጹም ቅጣት ምት ግብ አዲስአበባ ከተማን 1-0 መርታት ችሏል።

ልደታ ክ/ከተማ 1-0 አዳማ ከተማ

08፡00 ሲል በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ 25 ደቂቃዎች ለተመልካች ማራኪ የሆነ ብርቱ ፉክክር ሲያስመለክተን የመጀመሪያው የተሻለ ሙከራም 15ኛው ደቂቃ ላይ በአዳማዎች በኩል ተደርጓል። ሔለን እሸቱ ከቀኝ መስመር ከቅጣት ምት ያደረገችውን ሙከራ ግብጠባቂዋ አክሱማዊት ገ/ሚካኤል ስታስወጣባት ልደታዎች 20ኛው ደቂቃ ላይ ባልተጠበቀ እና ማራኪ በሆነ ቅብብል በወሰዱት ኳስ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። መዓዛ አብደላ ከሳጥን ውጪ አክርራ የመታችው ኳስ ድንቅ ግብ ሆኖ መረቡ ላይ አርፏል። አዳማዎች እንዳላቸው የኳስ ቁጥጥር የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲቸገሩ 38ኛው ደቂቃ ላይ ግን በቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ ውስጥ የማትጠፋው ሳባ ኃ/ሚካኤል ከግራ መስመር ያደረገችው ሙከራ ነጥሮ መረቡ ላይ ሊያርፍ ሲል በግብጠባቂዋ አክሱማዊት ገ/ሚካኤል እና በግቡ አግዳሚ ሲመክንባት በሦስት ደቂቃዎች ልዩነትም ሔለን እሸቱ ከሳጥን ውጪ ጥሩ ሙከራ ማድረግ ችላ ነበር።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው እጅግ አሰልቺ ሆኖ ሲቀጥል ሁለት የግብ ዕድሎች ብቻ በልደታዎች ተፈጥረውበታል። በቅድሚያም 66ኛው ደቂቃ ላይ ዘነበች ዲርጎ ከቀኝ መስመር አመቻችታ ያቀበለቻትን ኳስ ያገኘቸው አለሚቱ ድሪባ ኳሱን ከግብጠባቂዋ ማሳለፍ ብትችልም በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ለጥቂት ሲወጣባት 91ኛው ደቂቃ ላይም ራሷ አለሚቱ ድሪባ ከግብጠባቂ ጋር አንድ ለአንድ ብትገናኝም ያደረገችውን ሙከራ ግብጠባቂዋ መሠረት ባጫ በእግሯ መልሳባት የግብ ዕድሉን ሳትጠቀምበት ቀርታለች። ጨዋታውም በልደታ ክ/ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

\"\"

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1-1 አርባምንጭ ከተማ

10፡00 ላይ በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ በተደረገው የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ለተመልካች ሳቢ የሆነ ብርቱ ፉክክር ተስተናግዶበታል። የመጀመሪያው ፈታኝ ሙከራም 11ኛው ደቂቃ ላይ በንግድ ባንኮች ሲደረግ ሎዛ አበራ የሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ያደረገችውን ሙከራ ግብጠባቂዋ ቤተልሔም ዮሐንስ መልሳባታለች። በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ የቻሉት ባንኮች 20ኛው ደቂቃ ላይም ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ሎዛ አበራ ከቅጣት ምት ድንቅ ግብ ማስቆጠር ስትችል 36ኛው ደቂቃ ላይም ንግድ ባንኮች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ሰናይት ቦጋለ አመቻችታ ያቀበለቻትን ኳስ ያገኘቸው አረጋሽ ካልሳ ያደረገችውን ሙከራ ግብጠባቂዋ ቤተልሔም ዮሐንስ ስትመልስባት ያንኑ ኳስ ያገኘቸው መሳይ ተመስገን ሳትጠቀምበት ቀርታለች። በጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት በሚያገኙት ኳስ በቀጥተኛ ሽግግር የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የሚሞክሩት አርባምንጮች የመጀመሪያውን ለግብ የቀረበ ሙከራ 39ኛው ደቂቃ ላይ አድርገዋል። ቤተልሔም ታምሩ በቀኝ መስመር ከረጅም ርቀት በአስደናቂ ሁኔታ አክርራ የመታችው ኳስ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ተመልሶባታል።

ሆኖም ወደ ዕረፍት ሊያመሩ የዋና ዳኛዋ ማርታ መለሰ ፊሽካ ሲጠበቅ ቤተልሔም ታምሩ በግራ መስመር ከረጅም ርቀት ከቅጣት ምት ግብ አስቆጥራ አርባምንጭን አቻ ማድረግ ችላለች። ከዕረፍት መልስ በኳስ ቁጥጥሩ ንግድ ባንኮች ፍጹም የበላይነቱን ሲወስዱ የአርባምንጭን ተከላካዮች አልፈው ግብ ለማስቆጠር ግን እጅግ ተፈትነዋል። በተለይም ከእመቤት አዲሱ በሚነሱ እጅግ ማራኪ ኳሶች ወደፊት ለመጠጋት ቢሞክሩም አደገኛ ኳሶችን ወደ ሳጥን በመላክ እና የጠሩ የግብ ዕድሎችን በመፍጠር የምትታወቀው ሰናይት ቦጋለ ያልተለመደ ደካማ እንቅስቃሴ ለንግድ ባንኮች መፈተን ምክንያት ሆኖ ታይቷል። 66ኛው ደቂቃ ላይ ሎዛ አበራ 88ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ መዲና አወል ከሳጥን ውጪ በግራ እግራቸው ካደረጉት ሙከራ ውጪም የተሻለ የግብ ዕድል ሳይፈጠርበት ጨዋታው 1-1 ተጠናቋል።

\"\"