\”የበለጠ መስራት ይጠበቅብናል ፤ ካለው አጭር ቀን አንፃር ግን ያየነው ነገር መጥፎ አይደለም\” አሰልጣኝ ውበቱ አባተ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሩዋንዳ አቻው ጋር አዳማ ላይ ያደረገውን የአቋም መፈተሻ ጨዋታ 1-0 ካሸነፈ በኋላ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከጋዜጠኞች ጋር አጭር ቆይታ አድርገዋል።

የአጥቂ ክፍላቸውን አስመልክቶ…

\”እንደሚታወቀው አጥቂ ቦታ ላይ በርካታ ተጫዋቾችን ነው ያጣነው። አሁን ባለው ሁኔታ በዚህ የአጥቂ ቅንጅት ስንጫወት የመጀመሪያ ጨዋታ ነው ፤ አንድ ላይ ያልተጫወቱ ተጫዋቾች ናቸው በአብዛኛው። አማኑኤል ፣ ዳዋ እና አቡበከር በጉዳት የሉም። እነዚህን ተጫዋቾች አጥተን በአጭር ቀን ውስጥ ጥሩ ነገር ነው ያየሁት ፤ ምንአልባት አራት ቀን ቢሆን ነው ልምምድ ያደረግነው። የበለጠ መስራት የጠበቅብናል ፤ ካለው አጭር ቀን አንፃር ግን ያየነው ነገር መጥፎ አይደለም።\”

በመጀመሪያው ግማሽ የመከላከል ባህሪ ያላቸው አማካዮችን ስለመጠቀማቸው…

\”በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለት ሦስት የሚሆኑ ለጎል የቀረቡ ኳሶችን መድረስ ችለናል። ግን እዛጋ በትንሽ ዕርዳታ ወደ ጎል መቀየር የሚችሉ ኳሶች አቤል ለብቻው አግኝቷል ፣ ከነዓን ሁለት ጊዜ አግኝቷል ፣ ሽመልስ አግኝቷል ፤ እነዛን ወደ ጎል የመቀየር ሥራ መስራት እንዳለብን ይገባኛል። በመጀመሪያው አጋማሽ ይዘን የገባናቸው ተጫዋቾችም የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ናቸው። የጋቶች እና አማኑኤል መሀል ላይ መኖር ወደ መከላከሉ ያመዘነ ሊመስል ይችላል። ግን በጨዋታ አማኑኤል ከሳጥን ሳጥን መጫወት ይችላል ፤ ጋቶችም ያን ማድረግ ይችላል። ሌሎቹ ታፈሰ ፣ ሽመልስ እና ከነዓን ናቸው ፤ እነዚህም የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ናቸው። አቤልን ስንጨምር ከበቂ በላይ ነው። ብዙ ኳሶችን አግኝተናል። ከክፍት ጨዋታም ከቆመ ኳስም ዕድሎችን ፈጥረናል። ከሱሌይማን ከመስመር ላይ ያገኘናቸው አንድ የቆመ እና ከክፍት ጨዋታ የተገኙ ኳሶችን ስናይ ማጥቃቱም ላይ መጥፎ አልነበረም። ግን የመጨረሻው ሂደት በሙከራ መታጀብ አለበት። የጎል ዕድል የመፍጠር ንፃሬያችን ከፍ ማለት አለበት።\”

\"\"

ስለዮሴፍ ታረቀኝ..

\”ዮሴፍ ወጣት ልጅ ነው ፤ በዋናው ቡድን የመጀመሪያ ጨዋታው ነው። ጥሩ ነገር አለው ፤ በጣም ቀላል የሆነ ነገር ነው እንቅስቃሴው ላይ የሚታየው። በቀላሉ መዋሀድ ይችላል ብዬ አስባለሁ። ልጅ ስለሆነ ብዙ ብዙ ነገር የሚያሳየን ይመስለኛል። ግን የኢንተርናሽናል ጨዋታ ልምድ ባለማግኘቱ በአንድ ጊዜ ጫና ውስጥ እንዳንከተው መጠንቀቅ ያስፈልጋል። በተረፈ ግን ጥሩ ነገር እንዳለው ይሰማኛል።\”

ስለወጣት እና ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ምጣኔ…

\”የዮሴፍ ዓይነት ወጣት እና የመጀመሪያ ጨዋታው የሆነ አለ ፤ ሰዒድ በብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያው ነው። የዛኑ ያህል ደግሞ ልምድ ያላቸው እነጋቶች ፣ አስቻለው ፣ ይሁን ፣ ታፈሰ ሌሎችም አሉ። ሁለቱንም ያማከለ ቡድን ነው። ወጣቶቹ መምጣታቸው ደግሞ ከነባሮቹ ጋር ተቀናጅቶ የረጅም ጊዜ የብሔራዊ ቡድን ግልጋሎት የሚሰጡ ተጫዋቾችን ማፍራት ያስችለናል።\”

በግራ መስመር ተከላካይነት ሚሊዮን ሰለሞንን ስለመጠቀማቸው…

\”በአራት ተከላካይ ስንጫወት ሁለት የመስመር ተከላካዮች እና ሁለት የመሀል ተከላካዮችን ነው የምንጠቀመው። በአብዛኛው በዚህች አጭር ቀን ውስጥ መጥቶ ፍሌክሰብል ታክቲክ ለመጠቀም በሦስት ተከላካይ ለመጫወት ፣ በአራት አማካይ ለመጫወት ማሰብ ትንሽ በእኛ ሀገር ሁኔታ ያስቸግራል። ተጫዋቾቹም ከተለያየ ቡድን ከመምጣታቸው አንፃር ይህንን ነገር ቶሎ ይቀበሉታል ብለን አንገምትም። ግን ዛሬም ቢሆን የሚሊዮን እዛ ቦታ ላይ መጫወት ከረመዳን አለመኖር ጋር ነው የሚያያዘው። ረመዳን ሙሉ ጨዋታ የመጫወት ዕድሉን አላገኘም። የመጨረሻ ሚሊዮን በተጎዳበት ሰዓት ራሱ ጊትን አስገብተን ወደ ኋላ መልሰን ያጫወትነው ቸርነትን ነበር። ስለዚህ በግልፅ ለመናገር ከጉዳት ጋር የተያያዘ ነው። ረመዳን መጠነኛ የግጭት የጡንቻ ጉዳት ስላለው እንዲያገግም ለማድረግ ነው እንጂ ሌላ ነገር አስበን አይደለም። ያም ቢሆን ግን ሚሊዮንም ጥሩ ተጫውቷል ቦታው ላይ። በባህሪው የተለያየ ቦታ ላይ መጫወት ይችላል። በግራም በቀኝም በምቾት መጫወት ስለሚችል በጥሩ ሁኔታ ተወጥቶታል ብዬ መናገር እችላለሁ።\”

\"\"

የዛሬው ጨዋታ ለምርጥ 11 ፍንጭ ስለመስጠቱ…

\”ወደ 60 ደቂቃ ገደማ የመጀመሪያ ቅያሪያችንን አድርገናል። በይበልጥ ለምርጥ 11 የቀረቡ ተጫዋቾች ናቸው መጀመሪያ የገቡት።\”

ስለዑመድ ዑኩሪ…

\”ዑመድ ከቡድኑ ጋር ያልተቀላቀለው ትናንት በክለቡ ጨዋታ ስለነበረው ነው። ስለዚህ ወደዚህ መጥቶ ወደ ሞሮኮ ረጅም ጉዞ ከማድረግ እዛው ይቀላቀለናል። ስለዚህ የዑመድን ግልጋሎት ስለምናገኝ ሌላ ተጫዋች አንጠራም።\”

ከሩዋንዳ አንፃር ጊኒ ጠንካራ ተጋጣሚ ስለመሆኑ…

\”ጊኒ እና ሩዋንዳ አንድ አይደሉም። እኛ እና ጊኒም አንድ አይደለንም። ያም ቢሆን ግን ባሉት ተጫዋቾች ጥሩ ነገር ይዘን ለመምጣት ወደ ሜዳ እንገባለን።\”