\”ነገ የምንችለውን ነጥብ ለማግኘት የራሳችንን ዝግጅት አድርገናል\” ውበቱ አባተ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ከነገው ጨዋታ በፊት ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተዋል።

ለነገው ጨዋታ እያደረጉ ስላሉት ዝግጅት….

ከዓርቡ ጨዋታ በኋላ ተጫዋቾች ላይ ያየነው ክፍተት ከሥነ-ልቦና ጋር የተያያዘ ነበር። በዐምሮ ደረጃ በተለመደው መንገድ አልነበረም የተንቀሳቀስነው። ይህም በጊኒ የተወሰደብንን ብልጫ ሰፊ እንዲሆን አድርጎታል። እዚህ ላይ በጋራ እና በተናጥል ከተጫዋቾች ጋር ሰፊ ውይይት ማድረግ ላይ ነበር ትኩረት አድርገን ስንሰራ የነበረው። ተጫዋቾቹ ከነበረው ነገር ቶሎ ወጥተው ስለቀጣዩ ጨዋታ እንዲያስቡ ዝግጅታችንን ጨርሰናል። ከጤና ጋር ተያይዞ ሚሊዮን ሰለሞን በጉዳት ምክንያት ከጨዋታው ውጪ ሆኗል።

\"\"

ስለዓርቡ ጨዋታ እና ከጨዋታው በኋላ ስላለው አጭር የዝግጅት ጊዜ…

የትኛውም ውድድር ላይ ማሸነፍ፣ መሸነፍ እና አቻ ያለ ነው። ምናልባት ባልተለመደ መልኩ በጨዋታው ላይ የነበሩት እንቅስቃሴዎች እኛ በምንፈልገው መልኩ አለመሄዱ ተጫዋቾች ነገሮችን ለማድረግ ከነበራቸው ከፍተኛ ፍላጎት እና ጉጉት ነው የሚመስለኝ ፤ ይህንንም ነው ያየነው። ከተጋጣሚ ከደረሰው ብልጫ ወይም ጫና በላይ እኛ ጨዋታውን ለመቆጣጠር የሄድንበት መንገድ ልክ አልነበረም። ጨዋታው ያን ያህል ከባድ ሆኖ ሳይሆን ራሳችን የሰጠነው ግምትና ከጨዋታው የምንፈልገው ውጤት ጉጉት ላይ መሰረት ያደረገ ነበር። ጨዋታው ከዐምሮ ይልቅ አካላዊ ፍልሚያዎች የነበሩበት ጨዋታ ነበር። ለእነሱ የሚመጫቸው አቀራረብ ነው ሜዳ ላይ ያየነው። ተዘጋጅተን የገባንበት ጨዋታ ሳይሆን ስሜት ያመዘነበት ጨዋታ ነበር። ከዛ እንዲወጡ ለማድረግ በሰፊው ለመነጋገር ሞክረናል ፤ የዓርቡ ጨዋታ ለሁላችንም እስከዛሬ ከነበረው የመጨረሻ መጥፎ ጨዋታ ነበር። ከውጤት አንፃር ግን ምንም ማለት አይደለም ፤ በየትኛውም ሁኔታ ልታሸንፍ ልትሸነፍ ትችላለህ። ከእርሱ ይልቅ የነበረው እንቅስቃሴ ብዙ አስደሳች አልነበረም። ከዚህ ነገር እንዲወጡ ነው ያደረግነው። ቀኑ አጭር ቢሆንም ባለችው ቀን የምንችለውን ነገር ለመስራት ሞክረናል።

\"\" 


ከዓርቡ ጨዋታ መነሻነት የነገውን ጨዋታ ሊቀርቡ ስለሚችሉበት መንገድ…

የዓርቡን የመጀመሪያ አጋማሽ እንቅስቃሴ በተደጋጋሚ ለመመልከት ሞክረናል። የአቀራረብ ችግር ነበረብን ብዬ የምወስደው ብዙ ነገር የለም። ነገርግን ሜዳ ላይ የሚፈጠሩትን እያንዳንዱን ነገሮች ማየት ላይ በተለይ ዐምሯቸው ላይ የሳሉትን ነገር እና ሜዳ ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ነጣጥሎ አለማየት ችግር ነው ያየነው። ከነጥብ አንፃር በምድቡ ሁለት ቡድኖች 6 ሁለት ቡድኖች ደግሞ 3 ነጥን ነው ያለን ፤ እኛም ነገ የምንችለውን ነጥብ ለማግኘት የራሳችንን ዝግጅት አድርገናል።