​አምስት ግቦች በተቆጠሩበት ጨዋታ መከላከያ ቦሌን አሸንፏል

አመሻሽ ላይ የተደረገው የቦሌ ክፍለ ከተማ እና የመከላከያ ጨዋታ ጦሩን ከመመራት ተነስቶ አሸናፊ አድርጓል።

ጥሩ ፉክክር ማስመልከት የጀመረው የቦሌ ክፍለ ከተማ እና የመከላከያ ጨዋታ ሩብ ሰዓት ሲሞላው መሪ አግኝቷል። በዚህም ከመሐል ሜዳ የተመታውን ኳስ የግብ ዘቧ ሂሩት ደሴ ሰዓቷን ጠብቃ ባለመውጣቷ ንግስት በቀለ አግኝታው ቡድኗን መሪ አድርጋለች። ወደ ጨዋታው ለመመለስ ከአምስት ደቂቃ በላይ ያላስፈለጋቸው መከላከያዎች በ21ኛው ደቂቃ በገነት ኃይሉ አማካኝነት ባስቆጠሩት ግብ አቻ ሆነዋል። 26ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ መሳይ ተመስገን ከቅጣት ምት የመታችውን ኳስ የግቡ አግዳሚ ከግብነት አግዶታል።

 አሁንም ጫና መፍጠራቸውን የቀጠሉት መከላከያዎች ከመመራት ወደ መሪነት ተነስተው መሪ የሆኑበትን ጎል አግኝተዋል። በ28ኛው ደቂቃም ሴናፍ ዋቁማ ከሳጥን ውጪ የተረከበችውን ኳስ ተከላካዮችን አልፋ በድንቅ ሁኔታ በግራ እግሯ መረብ ላይ አሳርፋዋለች። መከላከያዎች በቀሪዎቹ ደቂቃዎችም ተጨማሪ ግቦችን ለማግኘት ቢጥሩም ሳይሳካላቸው አጋማሹ ተገባዷል።

 እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሳቢ ፉክክር ማስመልከት ያልቻለው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ያን ያህል የጠሩ የግብ ሙከራዎች አልነበሩበትም። በእንቅስቃሴ ደረጃም መከላከያ ኳስን ተቆጣጥሮ ለመጫወት ሲሞክሩ ቦሌዎች ደግሞ ለመከላከል ቅድሚያ በመስጠት በሚያገኟቸው የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች ግብ ፍለጋ ይዘዋል። 69ኛው ደቂቃ ላይ ግን ሁለተኛውን የቡድኑን ጎል በድንቅ ሁኔታ ያስቆጠረችው ሴናፍ በድጋሜ ከርቀት የቡድኗን ሦስተኛ ጎል በተመሳሳይ በሳቢ ሁኔታ አስቆጥራለች። 

ጨዋታው ከቁጥጥራቸው ውጪ የሆነባቸው ቦሌዎች ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ሊጠናቀቀ ሁለት ደቂቃ ሲቀረው ንግስት በቀለ ከቅጣት ምት በሞከረችው ኳስ የግብ ልዩነታቸውን ሊያጠቡ ነበር። ከደቂቃ በኋላ ደግሞ ንግስት በቀለ እና ጤናዬ ለታሞ በጋራ ከተከላካይ ጀርባ በመሮጥ እጅግ ለግብ የቀረበ ኳስ አግኝተው መስከረም ካንኮ አምክናባቸዋለች። በአጀማመሩ ብዙም የግብ ዕድል ያልተፈጠረበት ጨዋታም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ጥሩ መመላለስ ኖረበት ታይቷል። የዕለቱ ዳኛ ሲሳይ ራያ ያሳዩት አምስት ደቂቃዎች ሊገባደዱ ሲል ደግሞ ቦሌ ያገኘውን የቅጣት ምት አሻምተው የግቡ አግዳሚ ሲመልሰው ንግስት በቀለ በግንባሯ ግብ አድርጋዋለች። ጨዋታውም በመከላከያ ሦስት ለሁለት አሸናፊነት ተጠናቋል።

ልሳን የሴቶች ስፖርት ያዘጋጀው የቤቲካ የጨዋታ ኮከብ ተብላ ደግሞ የመከላከያን ሁለት ጎሎች ያስቆጠረችው ሴናፍ ዋቁማ ሆናለች።

ሊጉ ነገ በአርቴፊሻል ሜዳ ሲቀጥል
አዲስ አበባ ከተማ ከ ባህርዳር ከተማ (3፡00)
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ (5፡00)
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ አርባምንጭ ከተማ (10፡00)