​ሀዋሳ እና አዳማ ከተማ ረፋድ ላይ የተደረጉትን የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች አሸንፈዋል

የ2014 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ረፋድ ላይ በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች በይፋ ተጀምሯል።

የዘንድሮ የውድድር ዓመት የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ውድድር ሀዋሳ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ባደረጉት ጨዋታ በይፋ ተጀምሯል። በሀዋሳ አርቴፊሻል ስታዲየም ሁለቱ ቡድኖች ጨዋታቸውን ከማድረጋቸው በፊትም የዕለቱ የክብር እንግዶች የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የውድድር ዳሬክተር አቶ ከበደ ወርቁ፣ የሴቶች እና ልማት ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ኢ/ር ጌታቸው የማነ ብርሃን እና የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ባህል ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ የስፖርት ዘርፍ ሀላፊ አቶ ጥላሁን ሀሜሶ ተጫዋቾቹን ሰላምታ ሰጥተዋል።

ተመጣጣኝ ፉክክር ማስመልከት የጀመረው የድሬዳዋ እና ሀዋሳ ከተማ ፍልሚያ ያን ያህል የጠራ የግብ ማግባት ሙከራ ሳይደረግበት ቢቀጥልም ኳስን ለመቆጣጠር መሐል ሜዳው ላይ የነበረው ፍልሚያ ጠንካራ ነበር። አልፎ አልፎም ሁለቱም ቡድኖች በፈጣን ሽግግሮች ቀዳሚ ለመሆን ሲጥሩ ቢታይም ኳስ እና መረብ የተገናኘው የመጀመሪያው አጋማሽ መገባደጃ ላይ ነበር። በዚህም ሀዋሳ ከተማዎች ከወደ ግራ በሚገኘው የመዓዘን ምት አካባቢ ያገኙትን የቅጣት ምት ሲያሻሙት የድሬዳዋ ተጫዋቾች በሚገባ ማፅዳት ተስኗቸው ቅድስት ቴቃ አግኝታው ከመረብ ጋር አዋህዳዋለች።

መሪ ሆነው የመጀመሪያውን አጋማሽ ያገባደዱት ሀዋሳዎች በሁለተኛው አጋማሽም በጥሩ ተነሳሽነት ቀርበው ታይተዋል። በዚህም በ56ኛው ደቂቃ በቁጥር በዝተው ሲያጠቁ ድሬዳዋ የግብ ክልል ጥፋት ተሰርቶባቸው የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። የፍፁም ቅጣት ምቱንም ህይወት ረጉ አበባየሁ ጣሰው ላይ አስቆጥራ ሁለተኛ ጎል አግኝተዋል። ሁለቱ ጎል ያልበቃቸው ሀዋሳዎች ከአምስት ደቂቃዎች በኋላም ዳግም ወደ ጎል ደርሰው ዙፋን ደፈርሻ ከሳጥን ውጪ መሬት ለመሬት አክርራ በመታችው ኳስ መሪነታቸውን አስፍተዋል።

ቀስ በቀስ ጨዋታው ከቁጥጥራቸው ውጪ እየሆነባቸው የመጣው ድሬዳዋዎች የመጀመሪያው አጋማሽ የነበራቸው ተነሳሽነት ወርዶ ታይቷል። ለተቆጠረባቸው ግብም ምላሽ መስጠት ተስኗቸው ጫናዎች በርክተውባቸዋል። ይባስ በ72ኛው ደቂቃ ከሳጥኑ ጫፍ የተገኘን የቅጣት ምት ሣራ ነብሶ በቀጥታ መትታው አራተኛ ግብ ሊቆጠር ቢቃረብም ኳሱን የግቡ አግዳሚ መልሶታል። በቀሪ ደቂቃዎችም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር ሀዋሳ ከተማ ሦስት ነጥብ እና ሦሰት ጎል አግኝቷል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ልሳን የሴቶች ስፖርት ያዘጋጀው የቤቲካ የጨዋታ ኮከብ ሽልማትን የሀዋሳ ከተማዋ ህይወት ረጉ አሸናፊ ሆና የተዘጋጀላትን ልዩ ዋንጫ ተረክባለች።

5:15 ሲል የጀመረው የአዳማ ከተማ እና አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ጨዋታ ደግሞ ገና በጊዜ ግብ ተቆጥሮበታል። በዚህም ጨዋታውን በጥሩ ተነሳሽነት የጀመሩት አዳማዎች በቀኝ መስመር ላይ ወደ አቃቂ የግብ ክልል አምርተው ግብ አስቆጥረው ተመልሰዋል። በዚህም ትዕግስት ዘውዴ በቀኝ የሳጥኑ ክፍል በመገኘት የደረሳትን ኳስ ሔለን ሙሉጌታ መረብ ላይ አሳርፋዋለች። ገና በጅማሮው ፈተና የገጠማቸው አቃቂዎች በቶሎ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ቢታትሩም ጠንካራውን የአዳማ የኋላ መስመር ሰብሮ መግባት ተስኗቸዋል።

ጨዋታው 28ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ሔለን እሸቱ በነፃ አቋቋም ላይ ሆና ከግራ መስመር የተሻገረላትን ኳስ በግንባሯ ለአዳማ ሁለተኛ ጎል አድርጋዋለች። ይህቺው አጥቂ በቀጣይ በደቂቃ ልዩነት ተጨማሪ የግብ ዕድል ፈጥራ የግቡ አግዳሚ በተከታታይ መልሶባታል። አጋማሹም በአዳማ ሁለት ለምንም መሪነት ተገባዷል።

አቃቂዎች በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ታትረው በመጫወት ከጨዋታው ነጥብ ይዞ ለመውጣት ቢሞክሩም የአዳማን የመልሶ ማጥቃት አልቻሉም። በተለይ በ70ኛው ደቂቃ ተቀይራ የገባችው ሔለን አባተ የሞከረችው ጥቃት ቡድኑን ወደ ጨዋታው የሚመልስ ነበር። የአቃቂ ግብ ፍለጋ ነቅሎ መውጣት የጠቀማቸው አዳማዎችም ፈጣን ሽግግሮችን በማድረግ ተጨማሪ ግቦችን ለማግኘት ተንቀሳቅሰዋል።

ጨዋታው ለውሃ እረፍት ሊያመራ አንድ ደቂቃ ሲቀረው ደግሞ ናርዶስ ጌትነት ላይ ጥፋት ተሰርቶ አዳማዎች የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። የፍፁም ቅጣት ምቱንም ምርቃት ፈለቀ አስቆጥራው አዳማ ሦስተኛ ጎል አግኝቷል። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው ደግሞ አዳማ በጊዜያዊነት የደረጃ ሰንጠረዡን የሚመራበትን አራተኛ ጎል በፅብሃት መሐመድ አማካኝነት አግኝቷል። በጅማሮው ግብ ያስተናገደው ጨዋታውም በመገባደጃውም ባገኘው ሌላ ግብ ታጅቦ ተጠናቋል።

በአዳማ ከተማ አሸናፊነት በተጠናቀቀው ጨዋታ ላይ ደግሞ ሔለን እሸቱ የቤቲካ የጨዋታ ኮከብ ተብሏ ከልሳን የሴቶች ስፖርት ሽልማቷን ተረክባለች።