አምስት ተጫዋቾች ከኮቪድ ነፃ ሆነው ልምምድ ጀምረዋል

ባሳለፍነው ሳምንት የኮቪድ-19 ቫይረስ ተገኝቶባቸው የነበሩት ወሳኝ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ተጫዋቾች ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸው ታውቋል።

በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ካሜሩን ለሚደረገው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በስፍራው ዝግጅቱን እያከናወነ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በኮቪድ-19 ምክንያት የተወሰነ ዝግጅቱ የተሟላ ሳይሆን ቆይቶ ነበር። ድረ-ገፃችን ከዚህ ቀደም ባስነበበችው ዘገባ 2 ተጫዋቾች እና አንድ የአሠልጣኝ ቡድን አባል በቫይረሱ ተይዘው እንደነበረ ከዛ ግን ከትናንት በስትያ በተደረገላቸው ምርመራ አገግመው ቡድኑን መቀላቀቸውን አመላክታለች። በመሐል ደግሞ ተጨማሪ አምስት ተጫዋቾች እና ሦስት የአሠልጣኝ ቡድን አባላት በቫይረሱ ተይዘው እንደነበረም አስነብባ ነበር።

 

አሁን ከስፍራው ባገኘነው መረጃ መሠረት ደግሞ ለአራት ቀናት ቀሳ ውስጥ የሰነበቱት ወሳኞቹ አምስት ተጫዋቾች በዛሬው ዕለት በተደረገላቸው ምርመራ ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸው ታውቋል። ይሄንን ተከትሎም ተጫዋቾቹ በዛሬው የቡድኑ ልምምድ ላይ ተሳትፈዋል።