“በአንድነት ስሜት የምትንቀሳቀስ ከሆነ ውጤቱ የማይመጣበት ምክንያት የለም” – አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሚካፈልበት የካሜሩን የአፍሪካ ዋንጫ አስቀድሞ የእግርኳሱ ሰው ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው መልዕክት አላቸው።

በመሰረተችው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ላይ ተሳታፊ መሆን የሰማይ ያህል ርቋት የቆየችው ኢትዮጵያ ከ31 ዓመት በኋላ በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በሚመራው ቡድን ወደ አፍሪካ ዋንጫ መመለሷ ይታወሳል። ወደ ውድድሩ ከተመለስን በኋላም ‘ዳግመኛ በየሁለት ዓመቱ እንሳተፋለን ወይስ እንደቀድሞ ሌላ ሠላሳ አንድ ዓመት ልጠብቅ ነው ?’ የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነበር። ሆኖም ጊዜው ደርሶ በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ እየተመራች ኢትዮጵያ ዳግመኛ ወደ መድረኩ ከስምንት ዓመት በኋላ ብቅ ብላለች። በምድብ ሀ የተደለደለችው ኢትዮጵያ ከሁሉም ተሳታፊ ሀገራት በመቅደም ጨዋታዎቹን ወደምታደግበት ያውንዴ ከተማ በመግባት ዝግጅቷን በማድረግ ላይ ናት። ጥር አንድ የመጀመርያው ጨዋታ ከኬፕቨርዲ ጋር ከመደረጉ አስቀድሞ ያላቸውን ተሞክሮ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ ለአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው የተለያዩ ጥያቄዎችን አንስተንላቸው ተከታዩን ምላሻቸውን ሰጥተውናል።

ከዓመታት በፊት ከ31 ዓመት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ መግባት ስሜቱ ምን ይመስል ነበር ?

በወቅቱ የነበረውን ስሜት መግለፅ በጣም ከባድ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ለእግርኳስ ያለውን ፍቅር በግልፅ ያሳየበት ነበር። ልጆቼ ከቀድሞ ከ31 ዓመት በፊት የአፍሪካ ዋንጫ ከገባው ትውልድ ያልተወለዱ ናቸው። የነበረው ባህል የመሸነፍ ከማጣርያ የመውደቅ እና ሌሎች ነገሮች ነበሩ። ሆኖም ግን ይህን ሰብሮ በማለፍ ከ31 ዓመት በኋላ በእነርሱ አማካኝነት ሲሳካ የነበራቸው ደስታ የኢትዮጵያ ህዝብ የነበረው ደስታ ትልቅ ነበር። ሁሉም ሰው ተደስቷል እኔም በራሴ የአፍሪካ ዋንጫ ስመኘው የነበረው ነገር ነው። ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ መሆን እንደ ተራራ ሲታይ ቆይቷል። የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ለመሆን 21 ዓመት ወስዶብኛል። እና እንደ ግዙፍ ተራራ ዳገት ሚሆነውን ነገር አሰልጣኝ ተብለህ እንደገና ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፍ ትልቅ ነገር ነው።

በደቡብ አፍሪካ በነበራችሁ ቆይታ ስላደረጋችሁት ሦስት ጨዋታዎች ምን አስተያየት አለዎት ?

ቡድኑ ጠንካራ ነበር ማለት እችላለሁ። አሁንም ቢሆን ጠንካራ ነው። ሁላችንም በወቅቱ አንድ የሆነ ደረጃ ላይ እንደርሳለን የሚል ሙሉ ዕምነት ነበረን። አይደለም አፍሪካ ዋንጫ ለዓለም ዋንጫም ያልፋል ሚል ዕምነት ነበረን። ነገር ግን እዛ በሄድን ጊዜ ከዛምቢያ በኋላ የነበሩ ጨዋታዎች ቡድኑን ሚገልፁ አልነበሩም። በተለይ ከቡርኪናፋሶ ጋር በነበረው ጨዋታ መሐሉን በሚገባ የያዙት አዳነ ግርማ እና አስራት መገርሳ ሁለቱም ተጎድተው ሲወጡ ያ ቦታ ፈረሰ ማለት ነው። እነሱን የሚተካ ሰው ቢገባም ልጆቹም ስሜታዊ ነበሩ። ራሳቸውንም ማሳየት ይፈልጉ ስለነበር ከዛ በኋላ የመጣ የታክቲክ ፍላጎት ነበር። ያው እንዳየኸው አራት ለዜሮ ተሸነፍን የማለፍ ዕድላችን አከተመ። እሱም ብቻ ሳይሆን ሳላሀዲን ዛምቢያ ላይ የሳታት የፍፁም ቅጣት ራሷ አስገራሚ ነበረች። ሽመልስም ከቡርኪናፋሶ ጋር ስንጫወት በአምስትኛው ደቂቃው ላይ የሳተው ኳስ ራሱ ቢገባ ኖሮ ሙሉ በሙሉ የእግርኳሱን እንቅስቃሴ ይቀይረው ነበር። ይህም ሆኖ ብዙ ልዩነት ጫና ሳይኖር የአስራት እና የአዳነ መውጣት ቡድኑ ተሰበረ በቃ ፤ ከዛ አራት ለዜሮ ተሸነፍን ምንም ማድረግ አልቻልንም። ቀጣይ ከናይጀሪያ ጋር ነበር መውደቃችንን አረጋግጠን ስለነበር የገቡትንም ያልገቡትን ልጆች ጨማምረን ገብተን ሁለት ለባዶ ተሸንፈን ወጥጠናል። ይሄ በአፍሪካ ዋንጫ የመጀመሪያ ልምዳቸው ነው። እነዚህ ልጆች ከዛምቢያ ጋር እንደዛ መጫወታቸው በራሱ ምን ያህል ጉጉት እንደነበራቸው የሚያሳይ ነው። ከዛ በኋላ የሆነው ይህ ስብስብ እንዲቀጥል ከማድረግ ይልቅ እንዲፈርስ ነው የተደረገው። ባሬቶ የያዘው ከዛም ዮሃንስ ሳህሌ የያዘው ከሁለት አንዱን ሊያሳኩት ይችሉ ነበር። በሙሉ ዕምነት መናገር እችላለሁ በተለይ የባሬቶ ቡድን ባያፈርሱት ኖሮ ማሳካት ይቻል ነበር። ነገር ግን ቡድኑን ማፍረስ ነው የተፈለገው። እኔን አስወጡኝ ከዛ በኋላ ቡድኑን አፈረሱት። ከፈረሰ በኋላ በአዲስ መልክ ነው የመጡት ከዛም በኋላ ውጤቱም ብዙም የሰመረ አይደለም።

ሌላ ሠላሳ አንድ ዓመት ሳይጠብቅ ከስምንት ዓመታት በኋላ የአፍሪካ ዋንጫን ስላሳከው ቡድን ምን ይላሉ…?

አሁን ያለው ቡድን ከጥቂት ተጫዋቾች በስተቀር ከሰላሳ አንድ ዓመት በኋላ የገባውን ቡድን እያየ ያደገ ብሔራዊ ቡድን ሲሆን እነ አቡበከርም ‘እኛ ይህን ቡድን እየደገፍን ነው ያደግነው’ ብለው በሚዲያም ሲናገሩ ሰምተናል። እነዚህ ልጆች አድገው ከ8 ዓመት በኋላ ይህ ውጤት መጥቷል እና እጅግ ሚያስገርም ነው። ትልቅ ለውጥም ነው ሠላሳ አንድ ዓመት አልወሰደም ፣ ሀያ ዓመት አልወሰደም ከስምንት ዓመት በኋላ የተገኘ ነው። እንግዲህ እንደዚህ ዓይነት ብቃት ያላቸውን ልጆች ይዞ ነው የተገባው። የእነዚህን ልጆች አንድነት እየተጠበቀ መዝለቅ ከተቻለ እንደተባለው በየሁለት ዓመቱ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ማለፍ ይቻላል።

በቅርብ ዓመታት ዳግም ወደ አፍሪካ ዋንጫ እንመለሳለን ብለው ያምናሉ ?

ባልጠብቅም ግን ይታለፋል። ምክንያቱም እኛ እኮ ማን ጠብቆን ነበር። አንዳንድ አስተያየቶች ‘ምድብ ድልድል ቢወጣ ኖሮ ሦስት አራት ቡድን ቢጫወቱ ኖሮ አያልፉም’ ይሉ ነበር። ዓለም ዋንጫን እኮ እነ ደቡብ አፍሪካን መተን አስቀርተናል። ድልድል ቢኖርም የፈለከው ዓይነት ነገር ቢኖርም ሁሉም ጨዋታ አንድ ነው። እነዚህ ልጆች የመጫወት ፍላጎታቸው የአንድነታቸው ጉዳይ ሲታይ አጣራጣሪ አልነበረም። ስለዚህ የማታልፍበት አንዳች ምክንያት አልነበረም። ዋናው ነገር ጠንካራ ቡድን ማለት ውህደት የፈጠረ ቡድን ማለት ነው። የሚተዋወቅ ቡድን ማለት ነው ፤ አለቀ። ያም ደሞ የፈጠረው ረዥም ጊዜ አብሮ መቆየት ነው። አሁን የኛ ቡድን አንድ ሁለት ሦስት አራት ዓመት ቢቆይ ኖሮ ሌላም ዕድሎች ይገጥመውት ነበር። ከዛ በኋላ ለሌሎችም መስመሩን ትቶ ያልፍ ነበር።

ብሔራዊ ቡድኑ በውድድሩ ከምድቡ ማለፍ ይችላል ?

ማቀድ እኮ ዋንጫም ይታቀዳል፤ ዝም ብለህ እኮ ደርሰህ ልትመለስ አትችልም፤ ማቀድ ትክክል ነው። ዕቅዱ ሊሳካም ላይሳካም ይችላል። እንዳልኩህ ማሳካት የሚቻለው በቡድኑ የሚሰሩ ስህተቶችን መቀነስ ሲችል ነው። የሚሳካው ተረባርቦ በአንድነት የሚፈጠሩ ስህተቶችንን ማረም ሲቻል ነው። በእግርኳስ ላይ በግልህ የምትንቀሳቀሰው ነገር የለም። ስለዚህ ዕቅድ ማቀዱ ትክክል ነው። ተሸንፌ ልመጣ ነው የምሄደው አይልም። ለዋንጫ ግማሽ ፍፃሜ ሩብ ፍፃሜም ማለት ይችላል። ልጆቹ ጥሩ ናቸው ፣ ጥሩ እንቅስቃሴ አላቸው ፣ ሰውነታቸው የተጠበቀ ነው ፣ የመተዋወቅ ነገር አላቸው ፣ ከትላልቅ ቡድኖች ጋር ተጫውተው አይተዋል ከነ ኮትዲቯር ጋና እና ደቡብ አፍሪካ ጋር እነዚህ ቡድኖች ቀላል ቡድኖች አይደሉም። ማሸነፍም መፈተንም ችለዋል። ከነዚህ ጨዋታ ውስጥ የተፈጠሩ ችግሮችን መሙላት ክፍተቶች ላይ ሰርተው ወደ ሜዳ መግባት ብቻ ነው። ይህን ካደረጉ ውጤት የማያመጡበት የተባለው ዕቅድ ማይሳካበት ምንም ምክንያት የለም።

ከባለፈው የአፍሪካ ዋንጫ ተሞክሮ አሁን ላለው ቡድን የሚያስተላልፉት መልዕክት ?

ሁሉም በኃላፊነት የሚሰጠውን በአግባቡ መወጣት ይገባዋል። ያለ አግባብ ብቻህን የምታደርገው በሙሉ ችግር ይፈጥራል። ተከላካዩ አንድ ለግሉ ሚሰጠው አሳይመንት አለ። በዛ ላይ ደግሞ አሰልጣኙ የሚሰጠው ታክቲክ ይኖራል። ስለዚህ በሚሰጣቸው ቦታ እያንዳንዱ ልጆች ያንን ማሟላት ከቻለ እና በህብረት አንድ ሆነው የአሰልጣኝ ትዕዛዝ የሚያከብሩ ከሆነ እንዲሁም የጓደኛህን ባህሪ አውቀህ ከተረዳህው ባለው ችግር ክፍተቱን የምትሞላ ከሆነ እና በአንድነት ስሜት የምትንቀሳቀስ ከሆነ ውጤቱ የማይመጣበት ምክንያት የለም።