የአፍሪካ ዋንጫ ልዩ ዘገባ ከካሜሩን…

በካሜሩን አስተናጋጅነት ዛሬ በድምቀት የሚጀመረውን የአፍሪካ ዋንጫ አስመልክቶ ሶከር ኢትዮጵያ ከስፍራው በልዩ ዘገባዋ መረጃዎችን ወደ አንባቢዎቿ ማድረስ ጀምራለች።

ከሁለት ሳምንት በፊት የመጀመርያው ጉዞ በማድረግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድኑ አባላትን ያውንዴ የደረሱ ሲሆን ባሳለፍነው ሐሙስ ደግሞ የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ አባላትን እና የጽሕፈት ቤት ኃላፊዎችን ያካተተ ልዑክ ያውንዴ መግባቱ ይታወቃል። በትናንትናው ዕለት ደግሞ በፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ የሚመራ የስራ አስፈፃሚ አባላት እንዲሁም በአቶ ክፍሌ የሚመራ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የቦርድ አመራሮች እና በእግርኳሱ ለረጅም ዓመታት ድጋፍ ሲሰጡ የነበሩ ደጋፊዎች እና የሚዲያ አካላት በኢትዮጵያ ዐየር መንገድ አማካይነት ካሜሩን ያውንዴ ደርሰዋል።

 

በበረራው ወቅት በሲሳይ አድርሴ ፕሮሞሽን አማካኝነት የተዘጋጀው “መልካም ዕድል ለብሔራዊ ቡድናችን” የሚል ፁሁፍ ያረፈበት ኬክ በክቡር ፕሬዝደንቱ አቶ ኢሳይያስ ጂራ እና በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው አማካኝነት የኢትዮጵያ ብሔራዊ የህዝብ መዝሙር ተዘምሮ ተቆርሷል።

በጉዞው ውስጥ የዋልያዎቹ አለቃ ውበቱ አባተ ባለቤት ወ/ሮ ውብዓለም ወረደወርቅ እና የቅርብ ጓደኛቸው አቶ ተድላ በላቸው የጉዞው አካል በመሆን ታድመዋል። ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር የመጀመርያውን ጨዋታ ዛሬ የሚያደርጉት የኬፕ ቨርድ ደጋፊዎች ከኢትዮጵያውያን ተጓዦች ጋር አብሮ በመሆን ጥሩ ጊዜን ሲያሳልፉ አይተናል።

በዚሁ ጉዞ ውስጥ በምድብ ተደልድላ የምትገኘው ሀገር ኮሞሮስ ፕሬዝደንት አብረው በመጓዝ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድነ መልካም ምኞታቸውን ሲገልፁ ነበር። ከአራት ሰዓት በረራ በኋላ ያውንዴ የደረሰው የልዑካን ቡድንን የፌዴሬሽኑ ም/ፕሬዝደንት አቶ አበበ ገላጋይ እና የፕሮቶኮል ክፍል ጀላፊ አቶ ሚካኤል በመሆን ለልዑክ ቡድኑ አቀባበል አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ምሽት ላይ ዛሬ ጨዋታውን በሚያደርግበት ኦሌምቤ ስታዲየም ልምምዱን አከናውኗል። ሶከር ኢትዮጵያም እያንዳንዱን የአፍሪካ ዋንጫ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እንቅስቃሴ የተመለከቱ መረጃዎች ከስፍራው ማቅረቧን ትቀጥላለች።