​ነገ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሚያደርገውን ጨዋታ የሚመሩ ዳኞች ታውቀዋል

በአፍሪካ ዋንጫው ነገ ምሽት ኢትዮጵያ እና ኬፕ ቨርዴ የሚያደርጉትን ወሳኝ ጨዋታ የሚመሩ ዳኞችን ዝርዝር ሶከር ኢትዮጵያ አግኝታለች።

33ኛው የአህጉራችን ትልቁ የሀገራት ውድድር በካሜሩን ነገ እንደሚጀመር ይታወቃል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም በዚህ ውድድር ላይ የሚሳተፍ ሲሆን በምድብ አንድ አዘጋጇ ካሜሩንን ጨምሮ ከኬፕ ቨርድ እና ቡርኪና ፋሶ ጋር ተደልድሏል። የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታውንም በነገው ዕለት የሚያከናውን ይሆናል።


የኢትዮጵያ እና የኬፕ ቨርድ ፍልሚያ በኦሊምቤ ስታዲየም ሲከናወን ጨዋታውን የሚመሩ የመሐል እና ረዳት እንዲሁም የቫር ዳኞች ተለይተው ታውቀዋል። በዚህም አንጎላዊው ሄልደር ማርቲንስ ዲ ካርቫልሆ ጨዋታውን በመሐል አልቢትርነት ሲመሩ የሀገራቸው ልጅ ጄርሰን ኢሚሊያኖ ዶስ ሳንቶስ እና ከሲሸልስ የመጡት ጀምስ ፍሬድሪክ ኢሚል በረዳት ዳኝነት ተሰይመዋል። አልጄሪያዊው አቢድ ቻረፍ ሜሕዲ ደግሞ አራተኛ ዳኛ እንዲሆኑ ተመድበዋል።


በ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ላይ በሁሉም ጨዋታዎች ቪ ኤ አር ተግባራዊ እንደሚሆን ቀድሞ መነገሩ ይታወሳል። ታዲያ በዚህ መሳሪያ ላይ ሆነው የኢትዮጵያ እና ኬፕ ቨርድ ጨዋታን የሜዳ ላይ ዳኞቹን የሚረዱት ግብፃዊያኖቹ መሐሙድ ሞሐመድ አሹር እና መሐሙድ አህመድ ካሚል አቡልረጋ መሆናቸውን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።