የቀድሞው ተጫዋች የሰበታ ከተማ ቴክኒክ ዳይሬክተር ሆኗል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተካፋዩ ሰበታ ከተማ የቀድሞውን ግዙፍ አጥቂ በቴክኒክ ዳይሬክተርነት ወደ ክለቡ ቀላቅሏል።

በአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው የሚመሩት ሰበታ ከተማዎች በዘንድሮ የ2014 የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ አጀማመራቸው መልካም ካልሆኑ ክለቦች መካከል ይጠቀሳል፡፡ በአፍሪካ ዋንጫ ወቅት ፕሪምየር ሊጉ መቋረጡን ተከትሎ ቡድኑን ለማስተካከል የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ የሚገኘው ሰበታ ከተማ ቀድም ባለው ዘገባችን ረዳት አሰልጣኝ የሆኑት ብርሀን ደበሌ እና ዳንኤል ገብረማርያምን ስለማገዱ ገልፀን የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ደግሞ የቀድሞው አንጋፋ አጥቂ ፍቅሩ ተፈራን የቴክኒክ ዳይሬክተር በማድረግ ወደ ቡድኑ መቀላቀሉን ሶከር ኢትዮጵያ ማረጋገጥ ችላለች፡፡

በአዳማ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጥቂት ዓመታት ካሳለፈ በኋላ በደቡብ አፍሪካ ፣ ቼክ ሪፐብሊክ ፣ ፊላንድ ፣ ባንግላዲሽ ፣ ቬትናም ፣ ማሌዢያ እና ህንድ በሚገኙ የተለያዩ ክለቦች በመጫወት የእግር ኳስ ህይወቱን የመራው የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ተጫዋች ፍቅሩ የእግር ኳስ ማሰልጠኛ ማዕከል ከፍቶ ለመስራት ውጥን እንዳለው ከዚህ ቀደም ከድረገፃችን ጋር ባደረገው ቆይታ ገልፆ የነበረ ሲሆን አሁን ደግሞ የሰበታ ከተማ ክለብ የቴክኒክ ዳይሬክተር ሆኖ ክለቡን ስለመቀላቀሉ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡