ሀምበሪቾ የሦስት ተጫዋቾችን ዝውውር አጠናቋል

በቀጣዩ የውድድር ዘመን በፕሪምየር ሊጉ የሚሳተፈው ሀምበሪቾ ዱራሜ የሦስት ተጫዋቾች ዝውውር አገባዷል።

በፕሪምየር ሊጉ ላይ የመጀመሪያ ዓመት ተሳትፎን በቀጣዩ ዓመት የሚያደርገው የአሰልጣኝ ደጉ ዱባሞው ሀምበሪቾ ዱራሜ ከሰሞኑ ወደ ዝውውሩ በመግባት ሦስት ተጫዋቾችን ያስፈረመ ሲሆን በዛሬው ዕለትም ሦስት አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈርሟል።

ንጋቱ ጉዴቦ የክለቡ አራተኛው ፈራሚ ነው። ባሳለፍነው የውድድር ዓመት በየካ ክፍለ ከተማ የነበረው ተከላካዩ ሀምበሪቾን ምርጫው ሲያደርግ ፣ ከደደቢት ተስፋ ቡድን ከተገኘ በኋላ በዋናው ቡድን እንዲሁም በመድን እና በገላን የተጠናቀቀውን ዓመት ያሳለፈው የመስመር አጥቂው አፍቅሮት ሰለሞን እና በየካ ክፍለ ከተማ በተከላካይ ስፍራ ሲጫወት የነበረው ዲንክ ኬር አዳዲሶቹ የክለቡ ተጫዋቾች ናቸው።