​ሪፖርት | ጅማ አባ ጅፋር የመጀመሪያ ድሉን አሳክቷል

የዳዊት እስጢፋኖስ ግሩም የቅጣት ምት ጎል ጅማ አባ ጅፋርን ከድል ጋር አስታርቃለች

በፀሀያማው አየር ቀዝቀዝ ብሎ በጀመረው ጨዋታ ጅማ አባ ጅፋሮች የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ይዘው ታይተዋል። በቀዳሚዎቹ አስር ደቂቃዎች አማካዮቹ ዳዊት እስጢፋኖስ እና መስዑድ መሀመድ ከሳጥን ውጪ እምብዛም አደገኛ ያልሆኑ ሙከራዎችም አድርገው ነበር። ከኳስ ጀርባ የሆኑት አዲስ አበባዎቹ ቀስ በቀስ የቀጥተኛ ጥቃታቸው መታየት ጀምሮ የመጀመሪያውን አደገኛ ዕድል ፈጥረዋል። 12ኛው ደቂቃ ላይ እንዳለ ከበደ በረጅሙ የተላከለትን ኳስ ከግራ መስመር አሻምቶ ፍፁም ጥላሁን በግቡ አፋፍ ላይ ለማግባት ያደረገው ጥራት በግብ ጠባቂው አላዛር ማርቆስ እና በተከላካዮች ርብርብ የመከነ ነበር።

ከሙከራው በኋላም የአዲስ አበባዎች ወደ ግራ መስመር ያደላ የማጥቃት ጥረት አመዝኖ ይታይ ነበር። በእርግጥ 22ኛው ደቂቃ ላይ ጅማዎች በአዲስ አበባ ሳጥን አቅራቢያ ያቋረጡት እና ዳዊት እስጢፋኖስ ያመቻቸውን ኳስ ኢዮብ ዓለማየሁ በቀኝ በኩል ገብቶ የሞከረበት አጋጣሚ ጥሩ የሚባል ነበር። 

አዲስ አበባዎችም 30ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት መልስ ወደ ሳጥን በላኳቸው የአየር ላይ ኳሶች አደጋ ለመፍጠር ተቃርበው ነበር። በቀሪዎቹ የአጋማሹ ደቂቃዎች ከባድ ሙከራዎች ባይታዩም የጨዋታው ፍሰት ቡድኖቹ የማጥቃት አጋጣሚዎችን እንዲፈጥሩ የፈቀደ ሆኖ ነበር። ጅማ በቀኝ መስመር አመዝኖ አዲስ አበባዎችም በቶሎ ወደ ፊት መድረስን ያለሙ ረጅም ኳሶችን በመጠቀም ጫና ለመፍጠር ሲጥሩ ቢታዩም አጋማሹ ያለግብ ተጠናቋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ጠንከር ባለ ፉክክር ጀምሯል። የጨዋታው የማጥቃት ምልልስ በጨመረባቸው በእነዚህ ደቂቃዎች አዲስ አበባዎች 48ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ጥላሁን ከግራ መስመር ይዞ በገባው ኳስ ንፁህ ዕድል አግኝተው ኢላማውን መጠበቅ ሳይችል አምክኖታል። የሁለቱም የማጥቃት ጥረት ሳጥን ውስጥ እየደረሰ ሲቋረጥ ቆይቶ ጅማዎችም ለግብ የቀረቡበት አጋጣሚ ተፈጥሯል። 61ኛው ደቂቃ ላይ በሽመልስ ተገኝ ተቀይሮ የገባው በላይ አባይነህ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታው ኳስ በዳንኤል ተሾመ ጥረት ግብ ከመሆን ድኗል።

በጨዋታ እንቅስቃሴ ኳስ እና መረብ አልገናኝ ብሎ ቢቆይም 78ኛው ደቂቃ ላይ ከቆመ ኳስ ግብ ተቆጥሯል። ዳዊት እስጢፋኖስ በግሩም ሁኔታ ከርቀት በቀጥታ ወደግብ የላካው የቅጣት ምት አዲስ አበባ መረብ ላይ አርፎ ጅማን ቀዳሚ አድርጓል። በዚህ የተነቃቁት ጅማዎች ከደቂቃ በኋላ በመስዑድ መሀመድ የሳጥን ውጪ ሙከራ ሌላ ግብ ለማግኘት ቢቃረቡም የግቡ አግዳሚ መልሶባቸል። የፍፁም ጥላሁን ተመሳሳይ የርቀት ሙከራም በአላዛር ሲመለስ ለማየት ሌላ አንድ ደቂቃ ብቻ ነበር ያስፈለገው። እነዚህ ሁነቶች በአምስት ደቂቃዎች ውስጥ መፈጠራቸውም ጨዋታውን አግሎት ታይቷል።

በቀሪ ደቂቃዎችም አዲስ አበባዎች አቻ ለመሆን ጥረት የማድረጋቸውን ያህል ጅማዎችም ሳያደገፍጉ ተጨማሪ ግብ ለማግኘት ተንቀሳቅሰዋል። ሆኖም ጨዋታው በዳዊት እስጢፋኖስ ጎል እንዲቋጭ ሆኗል።
በውጤቱ የደረጃው ግርጌ ላይ የሚገኘው ጅማ አባ ጅፋር ደረጃውን ባያሻሽልም የመጀመሪያ ድሉን አሳክቶ ነጥቡን አራት አድርሷል።