መድኖች ተከላካይ ለማስፈረም ተስማሙ

ኢትዮጵያ መድኖች ኬኒያዊውን ተከላካይ ለማግኘት ተቃርበዋል።

ወሳኝ ተጫዋቾቻቸው የለቀቁባቸው እና ቁልፍ ዝውውሮች ያደርጋሉ ተብለው የሚጠበቁት መድኖች በዝውውር መስኮቱ የውጪ ዜጋ ተከላካይ ለማስፈረም ተቃርበዋል። ከአዳዲስ ተጫዋቾች በተጨማሪ የነባር ተጫዋቾች ውል ያደሱት መድኖች አሁን ደግሞ ባለፈው የውድድር ዓመት በአርባምንጭ ከተማ ቆይታ የነበረውን ኬንያዊው ተከላካይ በርናንድ ኦቼንግ ለማስፈረም ከጫፍ ደርሰዋል።

ለአምስት ዓመታት ቪጋ እና ዋዚቶ ለተባሉ የሀገሩ ክለቦች ከተጫወተ በኋላ ያለፈው የውድድር ዓመት በአርባምንጭ ከተማ ያሳለፈው ይህ ተጫዋች ለሀገሩ ኬንያ ብሄራዊ ቡድን አምስት ጨዋታዎች ማድረግ ችሏል።

ባለፈው የውድድር ዓመት ለዋንጫ ተፎካካሪ የነበረ ጠንካራ ቡድን የገነቡት የሁለት ጊዜ የኢትዮጵያ ፕሪምየርሊግ ባለ ክብር አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ በለቀቁባቸው ቁልፍ ተጫዋቾች ምትክ ሌሎች ተጫዋቾችንም ያስፈርማሉ ተብሎ ይጠበቃል።