​በዓምላክ ተሰማ ወሳኙን የአፍሪካ ዋንጫ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ይመራል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ከሀገራችን በብቸኝነት በዳኝነት እየተሳተፈ የሚገኘው በዓምላክ ተሰማ በጉጉት የሚጠበቀውን ወሳኝ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ እንዲመራ መመረጡት ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

በኮቪድ-19 ምክንያት አንድ ዓመት ተገፍቶ ከጥር አንድ ጀምሮ በካሜሩን እየተከናወነ የሚገኘው የአህጉሪቱ ትልቁ ዋንጫ ውድድር 20 ቡድኖችን ጥሎ ወደ ወሳኝ ምዕራፍ መሸጋገሩ ይታወቃል። በዚህም ለፍፃሜ ለማለፍ ነገ እና ከነገ በስትያ ሁለት ተጠባቂ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች ይደረጋሉ። ከሁለቱ እጅግ ተጠባቂ ጨዋታዎች መካከል ደግሞ ነገ ቡርኪና ፋሶ እና ሴኔጋል የሚያደርጉትን የምሽት 4 ሰዓት ፍልሚያ ኢትዮጵያዊው ዳኛ በዓምላክ ተሰማ በመሐል አልቢትርነት እንደሚመራው ሶከር ኢትዮጵያ አውቃለች።

በኦሊምቤ ስታዲየም የሚደረገውን ጨዋታ በዓምላክ ከረዳት የመስመር ዳኞቹ ኢብራሂም አብደላ ሞሐመድ (ሱዳን) እና ጊልበርት ቼሪዮት (ኬንያ) እንዲሁም በአራተኛ ዳኝነት ከተመደቡት ሌላኛው ኬኒያዊ ፒተር ዋውሩ ካማኩ ጋር የሚመራ ይሆናል። አራቱ ዳኞች በሜዳ ላይ ይህንን ጨዋታ ሲመሩ ከሞሮኮ የመጡ ሦስት ዳኞች ደግሞ በቪ ኤ አራ ክፍል የበዓምላክ ረዳት ሆነው እንዲያገለግሉ ካፍ መርጧል።

በዓምላክ ከዚህ ቀደም ሴኔጋል ከጊኒ እንዲሁም ካሜሩን ከኮሞሮስ ያደረጉትን ጨዋታ በዋና ዳኝነት መምራቱ የሚታወስ ሲሆን ናይጄሪያ ከግብፅ እንዲሁም ግብፅ ከሱዳን ሲፋለሙ ደግሞ የመጀመሪያ የቪ ኤ አር ዳኛ ሆኖ አገልግሎ እንደነበር አይዘነጋም።