​የፕሪምየር ሊግ የግማሽ ዓመት የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት የሚከፈትበት ቀን ታውቋል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛ ዙር የተጫዋቾች የዝውውር ጊዜ መጠነኛ ማሻሻያ ተደርጎበት ክፍት የሚሆንበት ቀን ተገልጿል።

የኢትዮጵያ እግርኳስ የበላይ አካል የሆነው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የ2014 የፕሪምየር ሊግ ተጫዋቾቸ የክረምት የዝውውር መስኮትን ከሐምሌ 1 እስከ መስከረም 19 ድረስ ክፍት አድርጎ ለ83 ቀናት በርካታ ተጫዋቾች ዝውውሮችን ሲፈፅሙ እንደነበር አይዘነጋም። የግማሽ ዓመት የሊጉ ተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ደግሞ ከየካቲት 28 ጀምሮ እስከ መጋቢት 28 ድረስ እንደሚቆይ ቀድሞ የተገለፀ ቢሆንም አሁን መጠነኛ ማሻሻያ እንደተደረገበት ድረ-ገፃችን አረጋግጣለች።


በቤትኪንግ ስያሜ እየተከናወነ የሚገኘው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የአምስት ሳምንታት ቀሪ ጨዋታዎችን በምስራቁ የሀገራችን ክፍል ድሬዳዋ አከናውኖ የመጀመሪያውን ዙር ውድድር እንደሚያገባድድ ይታወቃል። የ15ኛ ሳምንት የመጨረሻ የጨዋታ ቀንም የካቲት 23 ተደርጎ የመጀመሪያው ዙር እንደሚገባደድ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ጠቅሶ የዝውውር ጊዜውን ፌዴሬሽኑ መጠነኛ ማሻሻያ እንዲያደርግ ጥያቄ ባቀረበው መሠረት የዝውውር መስኮቱ ከየካቲት 24 ጀምሮ ለአንድ ወር ክፍት ሆኖ መጋቢት 24 እንዲዘጋ እንደተወሰነ ለማወቅ ችለናል። በተጠቀሰው ጊዜም የሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጪ የመጡ ተጫዋቾች በሙሉ መልቀቂያ እና የህክምና ማስረጃቸውን ይዘው ወደየ አዲሱ ክለባቸው መዘዋወር እንደሚችሉ ተመላክቷል።


የኢትዮጵያ እግርኳስ ድምፅ የሆነችው ሶከር ኢትዮጵያም የዝውውር መስኮቱ ከአንድ ወር በኋላ ተከፍቶ ለ30 ቀናት ሲቆይ የሚኖሩ የዝውውር እንቅስቃሴዎችን እየተከታተለች እንደምታቀርብ ከወዲሁ ለመግለፅ ትወዳለች።