አማኑኤል ገብረሚካኤል ፋሲል ከነማን በይፋ ተቀላቅሏል

ቀደም ብሎ ዐፄዎቹን ለመቀላቀል ተስማምቶ የነበረው አጥቂ በይፋ ቡድኑን ተቀላቅሏል።

ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለው ውል መጠናቀቁን ተከትሎ ለሙከራ ወደ ደቡብ አፍሪካ አቅንቶ የነበረው አማኑኤል ገብረሚካኤል ለፋሲል ከነማ ፊርማውን አኑሯል። ቀድም ብሎ በቃል ደረጃ ወደ ቡድኑ ለመቀላቀል ተስማምቶ የነበረው ይህ ተጫዋች በዛሬው ዕለት በይፋ ቡድኑን መቀላቀሉ ክለቡ አስታውቋል።

አጥቂው በዳሽን ቢራ፣ በሰሜን ሸዋ ደብረብርሀን፣ በመቐለ 70 እንደርታ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲሁም በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን መጫወት ችሏል። አሁን ደግሞ በሁለት ዓመት ውል ዐፄዎቹን መቀላቀሉ ተከትሎ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ካሰለጠኑት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በድጋሜ የመስራት ዕድል አግኝቷል።

ክለቡ ከምኞት ደበበ ጋርም ስምምነት መፈፀሙን ድረ-ገፃችን ከቀናት በፊት ዘገባ አቅርባ የነበረ ሲሆን የዝውውሩ መጠናቀቅንም ክለቡ በቅርቡ ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።