​የአሰልጣኞች አስተያየት | ሀዋሳ ከተማ 3-2 ድሬደዋ ከተማ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ሀዋሳ ከተማ ድሬዳዋ ከተማን ከረታበት የምሽቱ ጨዋታ በኋላ አሰልጠኞቹ ተከታዩን አስተያየት ለሱፐር ስፖርት ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ ዘራይ ሙሉ – ሀዋሳ ከተማ

ስለመጨረሻ ደቂቃዎች

“በመጀመርያ ፈጣሪ ይመስገን። በዛሬው ጨዋታ በእውነት ተፈትነናል። ከዕረፍት በፊት እንደፈለግነው አልተንቀሳቀስንም።
ከዕረፍት በኋላ ግን የታክቲክ ለውጥ በማድረግ ወደ ሦስት አምስት ሁለት ቀይሬ ነበር። እንደገና ተቀይረው በሚገቡ ልጆች ያንን ቦታ ሲዘጉብኝ ወደ አራት ሦስት ሦስት መለስኩና መጨረሻ ላይ መስመር አጥቂ በመቀየር የፊት አጥቂ በማስገባት ውጤቱ ተሳክቶልናል። በአሰልጣኝነት ህይወቴ የሚገርም ውጤት ነው ብዬ የማስበው።

ስለመስፍን ታፈሰ ጎል እና የደረጃ ሠንጠረጁ አናት ስለመጠጋታቸው

“ዛሬ ለዛም ነው ጉጉት እና ጭንቀት ውስጥ የገባነው ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥባችንን ለማጥበብ ነው። ይህ ስንመጣ ዋና ዕቅዳችን ነበር። ያ ደግሞ ባልጠበቅነው መንገድ ሁለት ጊዜ ተመራን ነገር ግን ልጆቼ በተለይ በግሉ መስፍን ሲያደርገው የነበረው በጣም የሚገርም ነበር። ወደ ፊት ትልቅ ተስፋ ያለው ልጅ ነው። በተለይ አንግል የመለሰበት ቢገባ ካገባው ይልቅ በጣም ደሰተኛ ያደርገኝ ነበር። ዞሮ ዞሮ ቡድኑ ውጤታማ እንዲሆን መስዋዕትነት ከፍሏል መስፍንን በዚህ መንገድ ነው የምገልፀው።

ስለድሬደዋ ቆይታቸው

“አንደኛ የኛ ቡድን ኳስ ይዞ የሚጫወት ቡድን ነው። እውነት ለመናገር ሜዳው ምቹ ነው። ሀዋሳ ላይ ሜዳው ምቹ ስላልሆነ የምናገኛቸውን ኳሶች አንጠቀምም ነበር። እዚህ ሜዳ ላይ ጎሎች ይገባሉ። የሜዳው ተፅዕኖ አለው ብዬ አስባለው። ከጨዋታ ጨዋታ ልጆቼ ራሳቸውን እያሳደጉ ስለመጡ በተሻለ እንገፋበታለን ብዬ አስባለሁ።”


አሰልጣኝ ፉአድ የሱፍ (ጊዜያዊ) – ድሬደዋ ከተማ

ውጤት ማስጠበቅ ስላለመቻላቸው

ከቆሙ ኳሶች ነው ፤ መዕዘን ምት የገቡብን ጎሎች። እዛ ላይ ሰርተን የተሻለ ውጤት እናመጣለን ብዬ ነው የማስበው። የመዘናጋት ነገሮች ናቸው ዋጋ ያስከፈሉን እዛ ላይ ጠንክረን እንሰራለን።

በማጥቃቱ በኩል ክፍተቶች አሉ

አይደለም የተሻለ ነገር አድርገናል። በማጥቃት ውጤት ይዘን ለመውጣት ያደረግነው ጥረት ያው የአጨራረስ ችግር ስለነበር ለዛ ተሸንፈን መውጣት ችለናል። ውጤቱን ለማስጠበቅ ያደረግነው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።

ሁለት አጋጣሚ ቀድሞ ጎል ማስቆጠራቹ አዘናግቷቹኋል ?

ሊሆን ይችላላል እርሱን እኔም እገምታለው። መዘናጋቱ በዛ የመጣ ይመስለኛል።

ቀጣይ ዕቅድ

ቀጣይ ላይ በደካማ ጎናችን ላይ ሠርተን የተሻለ ውጤት ለማስገንዘብ እንፈልጋለን። ልጆቼ ያሳዩት ብቃት የሚያስደስት ነው። የተሻለ እንቅስቃሴ አድርገዋል። መሸነፍ ውስጥ ማሸነፍ ስላለ ቀጣይ ላይ የተሻለ ነገር ሰርተን ህዝቡን ለማስደሰት እንሞክራለን።